አሜሪካ ከ 14 ዓመታት በኋላ የስጋ ምርት ወደ ቻይና መላክ ጀመረች

አሜሪካ ከ 14 ዓመታት በኋላ የስጋ ምርት ወደ ቻይና መላክ ጀመረች ።

እኤአ ከ 2003 በኋላ የመጀመርያዋ ስጋ የጫነች የአሜሪካ መርከብ ከቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ ደርሳለች፡፡

500 ፓውንድ የሚመዝን ስጋም ከ14 ዓመታት እገዳ በኋላ ከቻይና ሱፐርማርኬቶች ማግኘት ተችሏል፡፡

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው እገዳው የተነሳው፡፡

ባለፈው ግንቦት 11 ሁለቱ ሃገራት የአሜሪካ-ቻይና የ100 ቀናት የተግባር መርሃ ግብር ማዘጋጀታቸው ይታወሳል፡፡

በስጋ አቅርቦቱ ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱም የዚህ መርሃ ግብር አንድ አካል ነው፡፡

በዶሮ ተዋጽኦ ንግድ፣ በፋይናንስ እና የሃይል አቅርቦት ላይ በቀጣይነት ሁለቱ ሃገራት በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል፡፡

እገዳው ከመጣሉ በፊት አሜሪካ ከስጋ አቅረቦት ከፍተኛ ገቢ የምታገኘው ከቻይና ነበር፡፡

ዛሬም ቢሆን በቻይና ገበያ ከ8 ሚሊዬን ቶን በላይ የስጋ ፍላጎት ቢኖርም ሀገሪቱ ግን ከ6 ሚሊዬን ቶን በላይ አታመርትም፡፡

ቻይና ከፍተኛ የስጋ ምርት ወደ ሃገሯ በማስገባት በአለም ቀዳሚም ነች፡፡

በ2012 ዓም የ275 ሚሊዬን ዶላር ስጋ ወደ ሃገሯ ያስገባች ሲሆን እኤአ በ2016 ይህን አሃዝ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር አሳድጋዋለች፡፡

አሜሪካ በበኩሏ ቁጥር አንድ የስጋ አምራች ስትሆን ባለፈው አመት ብቻ ከ5.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስጋ ለዉጭ ገበያ አቅርባለች፡፡( ምንጭ: ዢንዋ)