የጣሊያን  የግብርና ዘርፍ  20 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ  ተገለጸ

ባለፈው አንድ ዓመት የጣልያን የግብርና ዘርፍ በ20 በመቶ እድገት ማሳየቱ  ተገለጸ ፡፡

ለእድገቱ መመዝገብ መንግስት ለዘርፉ የሠጠውን ትኩረት ያሳያል ተብሏል፡፡

ተፈጥሮአዊ የግብርና ዘርፍ የሚባለው ጥሩ ምርት ለማገኘት ሲባል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እና ሰው ሠራሽ ሂደቶችን ሳይጠቀም የሚካሄድ የግብርና አይነት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአለማችን ላይ ከ170 ሀገራት በላይ ተግባር ላይ ውሏል፡፡

የጣልያን የተፈጥሮአዊ ግብርና መረጃ ተቋም ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ በ2015 ተመዝግቦ የነበረውን የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተፈጥሮአዊ መንገድ ብቻ የለማ ሲሆን እኤአ በ2016 ደግሞ  20 በመቶ እድገት በማሳየት 1 ነጥብ 79 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተፈጥሮ ማልማት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በተለያዩ የግብርና ዘርፎች እድገት በማሳየት የአርሶ አደሮችም ቁጥር ከነበረበት ላይ በ20 ነጥብ 3 በመቶ እንዲያድግ በማድረግ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ ከ72 ሺ በላይ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩም ታውቋል፡፡

የጣልያን የግብርና ሚኒስትር ማውረቲዝዮ ማርቲና እንዳሉት ጣልያን የምትከተለው የግብርና ሂደት እና እያሳየችው ያለው ፈጣን የግብርና እድገት በአውሮፓ ከሚገኙ ሀገራት በሙሉ የሚልቅና አስተማማኝ ነው ብለዋል፡፡

በጣልያን የግብርና እድገት ላይ ከፍተኛውን አቅርቦት የሚሸፍነው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ሲሆን እኤአ በ2016 አመት ብቻ 48 ነጥብ 9 በመቶ ያደገ ሲሆን የጥራጥሬ ዘርፉ ደግሞ በ32 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማሳየቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የወይን እና የወይራ ውጤቶችም በግብርናው በፍጥነት ካደጉ ዘርፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

የጣልያን የተፈጥሮ ግብርና ፌዴሬሽን ፕሬዝዳት ፓውሎ ካርኔሞላ እንዳሉት የተያዘው አመት ባይጠናቀቅም እስካሁን ያለው የአሃዝ መረጃ እንደሚያሳየው በተፈጥሮአዊ መንገድ የሚለሙ መሬቶች እና የአርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል ኢ ኤስ ኤም እንደዘገበው፡፡