በቻይናና ሩሲያ መካከል ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ ተጀመረ

 

በቻይና እና በሩሲያ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ያጠናክራል የተባለው የተፈጥሮ ጋዝ የማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ  ኦፕሬሽን ሥራው መጀመሩ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

የተፈጥሮ ጋዝን ለቻይና በቀጥታ ተደራሽ ለማድረግ ቻይና እና ሩሲያ በተሰማሙት መሰረት ሩሲያ  የተፈጥሮ ጋዝ ለቻይና ለመላክ ለ 30 ዓመታት ሚቆይ ስምምነት እ.ኤ.አ ግንቦት 2014 ፈርማለች፡፡

 ይህ ደግሞ በሃይል ገበያ ላይ ቻይና ጋዝን በቀጥታ በተገነባ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ተጠቃሚ ስትሆን የመጀመሪያዋ እና ትልቋ ሃገር ያደርጋታል፡፡

የቻይናው ብሄራዊ የፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን እንዳስታወቀው የቻይናን እና የሩሲያን የኃይል ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዘው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ትቦ ግንባታ እየተፋጠነ ነው፡፡

በምስራቅ መንገድ የሚካሄደው የተፈጥሮ ጋዝ መስመር በሰሜናዊ ምስራቅ ሄይሎንግጂያንግ የሚነሳ ሲሆን ይህ ቧንቧ ከምስራቅ ቻይና ክፍል በሆነችው ሻንጋይ ያበቃል፡፡ እኤአ በሰኔ 2015 ጀምሮ የተጀመረው ግንባታ በ 2020 ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኩባንያው እንዳስታወቀው ከ3ነጥብ 371 ኪሎሜትር በምሥራቅ በኩል የተገነባው መንገድ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ የተገጠመው መሥመር ሥራውን ጀምሯል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ ቻይና በየዓመቱ 38 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ከሩሲያ ማግኘት ያስችላታል፡፡

ይህ ደግሞ የቻይና የኢነርጂ መዋቅርን ለማመቻቸት, የካርቦን ልቀት ለመቀነስ እና የአየር ጥራት እንዲሻሻል ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለውም ሲል የሃገሪቱ የመረጃ ምንጭ የሆነው ሲጂቲኤን በዘገባው አስነብቧል፡፡

በሩሲያ በኩል የሚካሄደው ግንባታ ደግሞ እኤአ በ2014 የተጀመረ ሲሆን ከምስራቅ ሳይቤሪያ ይነሳል፡፡

የድንጋይ ከሰልን ከመጠቀም ይልቅ የተፈጥሮ ጋዝን መጠቀም ጥሩ አማራጭ ሆኖ እንዲቀጥልም የሚያበረታታ ፕሮጀክት እንደሆነ የቻይና መንግስት ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሃገሪቷ የተፈጥሮ ጋዝን የሃይል ፍጆታን እኤአ በ2020  በ10 በመቶ ከፍ ለማድረግ እና በ2030 ደግሞ 15 በመቶ ከፍ ማድረግ እንዳለባት የቻይና ብሄራዊ የልማት እና የሪፎርሜሽን ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ( ምንጭ: ሲጂቲኤን)