ቻይና አዲስ የውጭ ኢንቨስትመንት ደንብ አወጣች

ቻይና  የውጭ ኢንቨስትመንቷን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል ደንብ አወጣች።  

ቻይና ካደጉና በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን  ግንኙኝነት ይበልጥ ለማጠናከር   የሚያስችል  አዲስ  የውጭ  ኢንቨስትመንት  ደንብ አወጣች ።

በመሆኑም ቻይና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በሀገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተቋማት አስተዳደራዊ ሂደቶችን ለማቀናጀትና ምጣኔ ሀብቱን ለማጠናከር አዲስ ህግ ማውጣቷን ይፋ አድርጋለች፡፡

እንደ ሀገሪቱ ብሄራዊ የልማትና ለውጥ ኮሚሽን አዲሱ ህግ  እ.ኤ.አ ከመጋቢት 2018 ጀምሮ በ2014 የወጣውንና እየተተገበረ ያለውን ህግ ተክቶ ሥራ ላይ ይውላል ነው የተባለው፡፡

በቀድሞው ህግ መሠረት ከ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለሚሆን ፕሮጀክት ጨረታ እንደሚወጣ እና ለድርጅቶቹም የተለያዩ መሥፈርቶች እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አዲሱ ህግ አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎችና ድርጅቶች የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት የቻይናን ብሄራዊ ጥቅም እና ደህንነት እንዲሁም  የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብትና የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን የማይጥሰ መሆን ይገባዋል ነው የተባለው፡፡

ቀላል እና ሳቢ እንደሆነ የተነገረለት ህጉ ድርጅቶቹ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ካሟሉ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት ይጓተት የነበረውን የአሠራር ሂደት ያቀለለ ነውም ተብሏል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም በአዲሱ ህግ መሰረት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም  መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የብድር መዝገቦችን፣ያልተገባ የገበያ ውድድርንና መደበኛ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ህጉ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡

የቻይና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በፈጣን እድገት ላይ ቢሆንም በዘርፉ ያልታሰቡና ምክንያታዊ ያለሆኑ መንገዳገዶች እንዳይደጋገሙ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በዘርፉ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው እና የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

በተለይም በሪልሰቲት፣ በሆቴልና በሲኒማ ቤት የሚደረጉት ኢንቨስትመንቶች ገደብ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል፡፡

ባለፉት 11 ወራት ውስጥ የቻይና ባለሃብቶች ከ 174 ሀገራት በተውጣጡ ድርጅቶች በጠቅላላው 107ነጥብ 55 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አውጥተዋል፡፡ በዋናነትም ለንግድ አገልግሎት ፣ለማምረቻ ኢንዱስትዎችና ለቴክኖሎጂ ዘርፎች የወጣው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ነው የተባለው፡፡(ምንጭ: ዠንዋና ሲጂቲኤን)