የሶሪያው ፕሬዝደንት በሽር አላሳድ የሩሲያ ወታደራዊ ካምፕን ጎበኙ

የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ የሩሲያ ወታደራዊ ካምፕን ጎበኙ   

የፕሬዝደንቱ ጉብኝት ሩሲያ ለሶሪያ የጦር ድጋፍ ማድረግ ከጀመረችበት ከ2015 ጀምሮ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

ጉብኝታቸውን ያካሄዱት የአሜሪካ መንግስት ለሶሪያ ማስጠንቀቂያ በሰጣት ማግስት መሆኑ ደግሞ ውዝግቡን አባብሶታል፡፡

የሶሪያው 19ኛው ፕሬዝደንት ባሻር ሀፌዝ አል አሳድ በአገሪቱ ምዕራባዊ አቅጣጫ ላታኪያ ግዛት የሚገኘውን ሜይም የሩሲያ ወታደራዊ ካምፕ ጎበኙ፡፡

ሞስኮ ለደማስቆ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ ከጀመረችበት እንደ አውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር ከ2015 ጀምሮ ይህ ወታደራዊ ስፍራ በፕሬዝደንቱ ሲጎበኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ሶሪያ ለገጠማት ቀውስ እና የተደራጀ የሽብር ጥቃት ከጀርባዋ በመሆን ሲያግዟት እና ጠላቶቼ ያለቻቸውን ልክ ሲያስገቡ የነበሩ የጦር ጄቶች በፕሬዝደንቱ ጉብኝት ወቅት ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡

አልፎ ተርፎም የሩሲያ ምርት የሆኑት ኤስዩ 35  የጦር ጄቶች በፕሬዝደንቱ ተጋልበዋል፡፡ ወታደራዊ ተልዕኮ ለመቀበል የተዘጋጁ የሚመስሉ የታጠቁ ወታደሮችን የጫኑ ተሸከርካሪዎችም አሳድን ለማጀብ ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ሩሲያ እንደ አይን ብሌኗ ከምትመለከታቸው እና ከምትመካባቸው የጦር ስፍራዎች መካከል ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነው ይህ የላታኪያ የጦር ካምፕ፤ በመካከለኛው ምስራቅ ላለው ቀውስ በተለይ ደግሞ ለደማስቆ ባለ ውለታ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ፕሬዝደንቱ አገራቸው መቋጫ ወዳልተገኘለት መናጥ ከገባች ወዲህ እንዲህ አይነት ጉብኝት ሲያካሂዱ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ በሰሜናዊው የደማስቆ ክፍል መታየታቸውም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው እሁድ በሃማ ተገኝተው ከዜጎቻው ጋር የኢድ በዓልን አክብረዋል፡፡

ነገር ግን የአሁኑን ጉብኝታቸውን ለየት ያደረገው፤ በሶሪያ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ለበርካቶች መቁሰል እና ከ80 በላይ ለሚሆኑት ሞት ምንያት የሆነውን የኬሚካል ጥቃት ተከትሎ ዋሽንግተን የአሳድን መንግስት መወንጀሏ ይታወሳል፡፡

በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ደግሞ ፔንታጎን የአሳድ መንግስት የኬሚካል ጥቃቱን ለመድገም በዝግጅት ላይ መሆኑን ሰምቻለሁ ማለቱን ተከትሎ ፕሬዝደንት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን እና ዋሽንግተን ሶሪያ ላይ የሚሳኤል ጥቃት እፈጽማለሁ ባሉበት ማግስት መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡

አሜሪካ በሶሪያ ሰማይ ላይ በጥምር ጦሯ አማካኝነት በነፃነት መንቀሳቀሷ፤ ለሩሲያ ሰላም አይሰጣትም፡፡

ሩሲያም አሳድን በጦር እና በቁሳቁስ መደገፏ ለነጩ ቤተ መንግስት ምቾት የሚነሳ መሆኑ አገራቱን በደማስቆ ጉዳይ ለዓመታት የጎሪጥ እንዲተያዩ አስችሏቸዋል፡፡

የአሁኑ የፕሬዝደንቱን ጉብኝት ሶሪያ የፔንታጎንን ጥርጣሬ እውን የምታደርግበት እና ለአሜሪካን ምላሽ የምትዘጋጅበት ለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ የትራምፕን የልብ  ምት የሚጨምር ትንታኔ የሚሰጡ አሉ፡፡

ሩሲያም ብትሆን የፕሬዝደንቱን ጉብኝት ምክንያት አድርጋ በሶሪያ ልሳነ ምድር ያሰፈረችውን ጦሯን ለመገናኛ ብዙሃኑ ያሳየችበት ነው የሚሉም አሉ፡፡

የፕሬዝደንቱ ጉብኝት እንደሚቀጥል የተነገረ ሲሆን ወደ የትኛው አቅጣጫ እንደሚያመሩ ግን የተገለፀ ነገር የለም፡፡  

ነገር ግን ቀጣዩ እርምጃቸውም አሜሪካንን የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ ሲሉ የዘገቡት አህራም ኦን ላይን እና ዘ ቴሌግራፍ ናቸው፡፡