ደቡብ ኮርያ በወታደራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሰሜን ኮርያ ጋር ለመወያየት ጥያቄ አቀረበች

ደቡብ ኮርያ ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰሜን ኮርያ ጋር  ለመወያያት ጥያቄ  አቀረበች ።

ውይይቱ ከተሳካ ፒዮንግያንግን በፀብ አጫሪነት ለሚከሱ አገራትም እፎይታን ይሰጣል ተብሏል፡፡ ፒዮንግያንግ ለሴዑል ጥያቄ እስከ አሁን የሠጠችው ምላሽ የለም፡፡

ደቡብ ኮርያ ባላንጣዋ ከሆነችው ሰሜን ኮርያ ጋር በወታደራዊ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት እንደምትፈልግ ገለፀች፡፡ ይህን ፍላጎቷንም ለፒዮንግያንግ አስታውቃለች፡፡

ሴዑል ጥያቄዋ በፒዮንግያንግ ተቀባይነት ካገኘ በመሪዎች ደረጃ በሁለቱ አገራት መካከል ከሶስት ዓመት በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ውይይት ይሆናል፡፡ 

ውይይቱ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ የነገሰውን ወታደራዊ ውጥረትን ለማርገብና በሁለቱ ኮሪያዎች ድንበር አካባቢ መረጋጋት እንዲሰፍን በሚቻልበት ጉዳይ ዙርያ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን ከሰሜን ኮርያው አቻቸው ጋር በቅርበት በመነጋገርና በመመካከር በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙን ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ተደምጧል፡፡ ከሰሜኑ አቻቸው የሚፈልጉትን ዓይነት አጥጋቢ ምላሽ ባያገኙም፡፡ 

ፕሬዚዳንት ሙን በጀርመን በርሊን ባደረጉት ንግግር ለፒዮንግያንግ ያቀረቡት የእንነጋገር ጥያቄ ከዚህ ቀደም ካቀረቡት ጠንካራና ገፋ ያለ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ውይይቱ ከተሳካ ፒዮንግያንግ በተለያዩ ጊዜያት የምታደርገውን የሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ ከፀብ አጫሪነት ድርጊቷ እንድትታቀብ ለሚጥሩ አካላትም ጥሩ እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዲህ ቢሉም ታዲያ ሴዑል አሁን ላቀረበችው የእንነጋገር ጥያቄ እስከ አሁን ድረስ በፒዮንግያንግ በኩል የተሠጠ ምላሽ የለም፡፡  

የደቡብ ኮሪያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ሱ ቹ ሱክ በበኩላቸው በአገራቱ መካከል የሚደረገው ውይይት እኤአ ሐምሌ 21 2017 እንዲሆን ሴዑል ጥያቄ ማቅረቧን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ከፒዮንግያንግ አዎንታዊ ምላሽ እንጠብቃለን ነው ያሉት፡፡ 

ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብን በመተላለፍ በተለያዩ ጊዜያት ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ የሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ በዚህም ከመንግስታቱ ድርጅትና ከአሜሪካ ውግዘት እየቀረበባት ይገኛል፡፡