ጣይብ ኤርዶጋን የባህረ ሰላጤውን ቀውስ ለመፍታት ከሳውዲና ኩዌት ጋር ተወያዩ

በባህረ ሰላጤው ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ለማደራደር የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኢርዶጋን ከሳዑዲና ኩዌት ኢሚር ጋር ተወያይተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ከኳታር ኢሚር ጋር በመወያየት ለሁለት ቀናት በባህረ ሰላጤው ሀገራት የነበራቸውን ቆይታ ያጠናቅቃሉ፡፡

ኳታር ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከአንድ ወር በፊት ነበር ሙሉ በሙሉ የተቋረጠው ፡፡

ይህን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ጉዳዩ በሰላም እንዲፈታ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል ኩዌት፣ አሜሪካና ቱርክ ቀድመው ሀገራቱ ወደ ውይይት እንዲመጡ ሲወተውቱ የነበረ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትና ጀርመንም ቀውሱ እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ቀውሱ ከተፈጠረ ጀምሮ ቱርክ የባሀረ ሰላጤው ሀገራት ከኳታር ጋር ያላቸው ግንኙነት ወደ ቀደመው ሰላም እንዲመለስ ጥረት እያደረገች ነው፡፡

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኢርዶአን የቀውሱ አካል ከሆነችው በሳዑዲ አረቢያ ተገኝተው ከንጉስ ሳልማንና ከልዑል ሙሀመድ ቢን ሳልማን ጋር ቀውስ በሚፈታበት ሂደት የተናጠል ውይይት አካሂደዋል፡፡

ኢርዶአን በሳዑዲ ንጉስ ሳልማንን ባገኙበት ወቅት ሳዑዲ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አቅም እንዳላት አንስተዋል፡፡

ቱርክ በባህረ ሰላጤው ሀገራት የ17 ቢሊዮን ዶላር የንግድ እንቅስቃሴ ታካሄዳለች የአሁኑ የሀገሪቱ የማሸማገል ተግባርም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ዓላማ ያለው እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

አሁን የአውሮፓ ህብረትም ቢሆን ሀገራቱ ሰላም እንዲያወርዱ እና ወደ ቀደመ ሰላማቸው እንዲመለሱ እየወተወተ ነው፡፡ የህብረቱ ፕሬዝዳንት ሙጊሪኒም በተለይ ኬዌት እያደረገች ያለውን የማደራደር ተግባር ህብረቱ እንደሚደግፍ ነው የገለፁት፡፡

ኤርዶአን በሁለት ቀን የባህረ ሰላጤው ሀገራት ቆይታቸው ከሳዑዲ በመቀጠል ወደ ኩዌት ነው ያቀኑት፡፡ እናም ፕሬዝዳንቱ ዋና አደራዳሪ ከሆነችው የኩዌት ኢሚር ሺህ ሳባህ አል አህመድ አል ሳባህ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ኤርዶአን ከኢሚሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ቀውሱን ለመፍታት ምንም አይነት የዲፕሎማሲያዊ ሰዓት ማባከን እንደማይገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ኤርዶአን አሁን በባህረ ሰላጤው ሀገራት እያደረጉት ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው አስቀድመው አሁን በሀገራቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማስቆም የትኛውም ሀገር ቢሆን መፍቀድ እንደሌለበት አሳስበው ነበር፡፡

እሳቸው በንግግራቸው አክለውም ስማቸውን መጥራት ያልፈለጓቸው አካላት ወንድማማቾችን እያጋጩ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡ 

በዚህ የግጭት ወቅት ኳታር  ጉዳዩን በብስለት ለማጤን ያደረገችውን ሂደትንም እሳቸው አድናቆት ችረውታል፡፡

ኤርዶአን በባህረ ሰላጤው ሀገራት የነበራቸው የሁለት ቀን ቆይታ ከኳታሩ ኢምር ሺህ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ጋር ውይይት በማካሄድ ይጠናቀቃል ሲል ፡፡( ምንጭ :አልጀዚራ)