እስራኤል በምስራቃዊ እየሩሳሌም የገጠመችው የብረት ነክ መፈተሻን አነሳች

እስራኤል በምስራቃዊ እየሩሳሌም በሚገኘው የአል አቅሳ መስጊድ የገጠመችውን የብረት ነክ ቁስ መፈተሻ መሳሪያ አነሳች፡፡

እስራኤል መሳሪያውን ያነሳቸው ከዓለም አቀፍ አካላት እየደረሰባት ባለው የዲፕሎማሲ ጫና ምክንያት እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡

ከሰሞኑም በሁለቱ ተጎራባች ሀገራት መካከል አዲስ ግጭት መቀስቀሱ  ተመልክቷል ፡፡

አንድ የእስራኤል አረብ ዝርያ ያለው የታጠቀ ግለሰብ ሁለት የእስራኤል ፖሊሶችን መግደሉን ተከትሎ እስራኤል በእስልምና ቅዱስ ቦታ ሆኖ በሚያገለግለው የአል አቅሳ መስጊድ ጥበቃው እንዲጠናከር እያካሄደች ያለው ተግባር ለዚህ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል፡፡

በእርግጥ የፖሊሶቿን መገደል ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው አጸፋ አራት ፍልስጤማዊያንዊያን ህይወታችን እንዲያጡ ሆኗል፡፡

ሶስት ተጨማሪ እስራኤላዊያንም በምስራቅ እየሩሳሌምና በዌስት ባንክ አካባቢዎች በጩቤ ተወግተው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ባለበት እስራኤል በእስልምና እምነት ቅዱስ ቦታ ሆነው ከሚታዩት አንዱ በሆነው  የአል አቅሳ መስጊዲን ለመጎብኘት የሚመጡ ዜጎችን በጥብቅ ፍተሻ እንዲያልፉ ይደረጋል ማለቷ ቀውስ ይበልጥ እንዲያገረሽ ምክንያ ሆነ፡፡ 

በዮርዳኖስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማውያን እንደሚኖሩ  የሚገመት ሲሆን የእስራኤልን ውሳኔ ተቃውሞ ያሰሙት  ሁለት ዮርዳኖሳውያን በእስራኤል ኢምባሲ ፊት ለፊት በኢምባሲው ጠባቂዎች ተገድለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ሁለት ዜጎቿ የተገደሉባት ዮርዳኖስ ሌላ እስራኤል በአሁኑ ወቅት  ጠላትነት  ሆና ብቅ ያለች አገር ሆናለች ፡፡

እስራኤል አሁን በአል አቅሳ መስጊድ ለጥብቅ የብረት ነክ ፍተሻ የገጠመችውን መፈተሻ መሳሪያ ካላነሳች በዮርዳኖስ የሚገኙ የእስራኤል ዲፕሎማቶች ከሀገሯ እንዲወጡም ካሁኑ ማስጠንቀቂያ  ሠጥታለች ፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በዚህ ጉዳዩ ላይ  ለመምከር በስልክ ማውራታቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም አሁን በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል እየተካረረ የመጣው ግጭት በቶሎ መፍትሄ ካልተበጀለት ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ እልቂት እንደሚያመራ ስጋታቸውን አሰምተዋል፡፡

ሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ ልዑክ ባወጣው ሪፖርት አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ቀውስ እጅግ እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡

በተለይ እስከ መጭው አርብ እስራኤል የፍተሻ መሣሪያውን አስመልክቶ ውሳኔ ካላሳለፈች ችግሩ እንደሚባባስ አስጠንቅቆ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ዘግይቶም ቢሆን እስራኤል በቅዱሱነቱ በሚታወቀው የአል አቅሳ መስጊድ የገጠመችውን የብረት ነክ መፈተሻ መሳሪያ እንዲነሳ ወስናለች፡፡

የእስራኤል የፀጥታ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ካቢኒ ተገናኝቶ በወሰነው መሰረት ሀገሪቱ የገጠመችውን መፈተሻ  መሳሪያ ሙሉ በሙሉ በማንሳት ቀለል ባሉ የደህንነት ስራ በሚያከናውኑ ተግባራት እንዲከናወኑ ይደረጋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁን እስራኤል በአካባቢው ባላት የጸጥታ ስጋት ምክንያት በምትኩ በርከት ያሉ የፖሊስ ኃይሎችን እንደምታሰፍር አስታውቃለች፡፡