ሱዳንና ዮርዳኖስ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ሱዳን እና ዮርዳኖስ በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ ።

በፊርማው ስነ ስርዓት ላይ በአስር የተለያዩ የስራ መስኮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በኪር ሃሰን ሳሊህ እና የዮርዳኖሱ አቻቸው ሃኒ አል ሙሊክ ከሁለቱም ሃገራት ከፍተኛ ኮሚቴዎች ጋር  በተደረገው የጋራ ውይይት ላይ ነው፡፡

በካርቱም በተደረገው በዚሁ ስምምነት ሱዳንና ዮርዳኖስ በምጣኔ ሃብት፣ በትምህርት፣ በአገልግሎት  ዘርፎች በጋራ በመስራት የሁለቱንም ሃገራት ወዳጅነት ያጠናክረዋል ተብሏል፡፡

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በኪር ሃሰን ሳሊህ ስምምነቱ የሁለቱንም ሃገራት ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም መሰረት ያደረገ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የተደረጉ ስምምነቶች የሃገራቱ ዜጎች ከሚጠብቁት በእጅጉ ያነሰ ነበር ብለዋል፡፡

የዮርዳኖሱ አቻቸው ሃኒ አል ሙሊክ በበኩላቸው ሃገራቸው የቀድሞው የሃገራቱን ስምምነት ለመተግበር ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡ 

የዮርዳኖሱ የንግድ እና ኢንዳስትሪ አቅርቦት ሚኒስትር ያሩብ ቃዳህ የሱዳን እና የዮርዳኖስ የንግድ ስምምነት በየዓመቱ ከ80 እስከ 120 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚደርስ ነው የጠቆሙት፡፡

በቀጣይ ሶስት ዓመታት ሁለቱም ሃገራት በጋራ ለመስራት የተስማሙባቸው ዘርፎች በትምህርት፣ ባህል፣ በወጣቶች፣ በማህበራዊ ልማት፣ በሙያ ስልጠና ፣ በኢንዱስትሪ ከተሞች፣ በታዳሽ ሃይል፣ በኤሌክትሪክ አቅርቦት እና በማዕድን ሃብት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት 228 የዮርዳኖስ ባለሃብቶች በሱዳን የመዋዕለ ንዋይ ስራዎችን እየሰሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 166 በማምረቻው ዘርፍ፣ 55ቱ በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም 17ቱ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ( ምንጭ  የዥንዋና ሱዳን ትሪቡዩን )