አሜሪካ ሰላም አስከባሪ ጦሯን ከአፍጋኒስታን እንደማታስወጣ ፕሬዚደንት ትራምፕ ተናገሩ

አሜሪካ ሰላም አስከባሪ ጦሯን ከአፍጋኒስታን እንደማታስወጣ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ ሃገሪቱ በአፍጋኒስታን ላይ የምትከተለውን የስትራቴጅ አቋም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደመንበረ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከተመረጡ የአሜሪካ ወታደሮችን ከአፍጋኒስታን ምድር በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ አደርጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተው እንደነበር ይታወቃል።

ፕሬዝደንቱ ዋሽንግተን በአፍጋኒስታን ላይ ስለምትከተለው ስትራቴጂካዊ አቋም በተመለከተ መግለጫ ሲሰጡ ግን የቀድሞ አቋማቸውን ለውጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 25 ደቂቃ በፈጀው መግለጫቸው አሜሪካ በአፍጋኒስታን ለማሸነፍ መዋጋት የሚል ስትራቴጅን እንደምትከተል ይፋ አድርገዋል፡፡

አሜሪካ ወታደሮቿን  ከካቡል ማስወጣት ማለት ለሽብርተኞች ክፍተት መፍጠር ነው ያሉት ፕሬዝደንት ትራምፕ ይህ ደግሞ የማይታሰብ ነው ብለዋል፡፡ እንደውም በአፍጋኒስታን አሸባሪዎችን ከአካባቢው ለማጥፋት ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃን መውሰድ ነው የምንከተለው ስትራቴጅና የተዘጋጀነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

የቀድሞ ፕሬዝደንቶች ከአፍጋኒስታንና ኢራቅ ወታደሮችን ለማስወጣት ይዘውት የነበረው ቀነ ገደብም ትክክል እንዳልሆነ የተናገሩት ትረምፕ መቼ ይወጣሉ የሚለውንም ጉዳይ አሁን ማሳወቅ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በካቡል ለ16 ዓመታት የዘለቀውን ግጭትን እልባት ለመስጠት የአፍጋኒስታን መንግስት፣ ፓኪስታን፣ ህንድ እና የኔቶ አባል ሀገራት በጋራ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ እንደታሊባንና የመሳሰሉ ጽንፈኞችን ለመዋጋት መወሰናቸውን ትረምፕ አስረድተዋል፡፡

ትራምፕ በመግለጫቸው ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ግጭት እንዲባባስ የምታደርገውን ጠብ አጫሪነት እንድታቆም አስጠንቅቀዋል፡፡

ኢዝላማባድ ለጽንፈኛ ኃይሎች ምሽግ መሆኗን ካላቆመችና ከአሜሪካ ጎን ቆማ ካልተዋጋች ዋጋ የሚያስከፍላት እርምጃ እንደሚጠብቃትም ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡

የፕሬዝደንት ትረምፕን ንግግር ተከትሎ ታሊባን በሰጠው ምላሽ አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ካላስወጣች በዛች ሃገር አንዳች የባሰ ችግር ይፈጠራል ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ኢዝላማባድ በበኩሏ በወታደራዊ ቃልአቀባያ በኩል በሃገሪቱ መሽጎ የተቀመጠ አሸባሪ የለም በሚል የአሜሪካን ወቀሳ ማጣጣሏ ነው የተነገረው፡፡

ፓኪስታን የትረምፕን ወቀሳ ብታጣጥልም እንግሊዝ የአሜሪካን አቋም እንደምትደግፍና በካቡል ሰላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ በመከላከያ ሚኒስትሯ ሚካኤል ፋሎን በኩል አረጋግጣለች፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን የሚገኙ ሲሆን አሜሪካና አጋሮቿ በአፍጋኒስታን ከአሸባሪዎች ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ በድል ለመቀዳጀት 4ሺ ወታደሮችን ለመጨመር መወሰናቸው እየተነገረ ነው፡፡

ምናልባትም ያሁኑ የአሜሪካና አጋሮቿ ስትራቴጅ በካቡል ያለውን ግጭት አስቁሞ ዜጎች የሰላም ስትንፋስ እንዲተነፍሱ ያደርጋል የሚለው የብዙዎቹ እምነት ነው ፡፡ ( ምንጭ: ቢቢሲና ሲኤን ኤን )