ኳታር በከፍተኛ ገንዘብ 24 ዩሮ ፋይተር ጀቶችን ከብሪታንያ ገዛች፡፡

ስምምነቱ በብሪታንያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያሥችልም ነው የተነገረው፡፡

ኳታር ከብሪታንያ ኩባንያ ጋር የደረሰችው የአሁኑ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት፥ ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ካደረገቻቸው የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነቶች ሁሉ ግዙፉ ተሰኝቷል፡፡

ስምምነቱን የብሪታንያ መከላከያ ዋና አዛዥ ጋቪን ዊሊያምሰንና የኳታሩ አቻቸው ካሊድ ቢን ሙሃመድ ናቸው በዶሃ ይፋ ያደረጉት፡፡

በስምምነቱ መሰረት ኳታር እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ ዩሮ ፋይተር ታይፉን ጀት የተሰኙትንና የዓለም የመጨረሻው የቴክኖሎጂ ግኝት አሻራ ያረፈባቸው 24 ተዋጊ ጀቶችን ከብሪታንያው የመከላከያና የኤሮስፔስ ኩባንያ (ቢኤኢ) የምትረከብ ይሆናል፡፡

በብሪታንያዋ ላንክሻየር ጀቶቹን ለመገጣጠም በሚደረገው የሥራ ሂደትም  ከ5 ሺህ በላይ  ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው በስምምነቱ ወቅት የተጠቀሰው፡፡

ዊሊያምሰን ስምምነቱ በብሪታንያ ከሚፈጥረው ሰፊ የሥራ ዕድል በተጨማሪ ምጣኔ ሀብትን በመደገፍ ረገድም ሚናው ላቅ ያለ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ሀገራቸው ከኳታር ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መመንደጉን የተናገሩት የመከላከያ አዛዡ፥ ከስምምነት የተደረሰባቸውን ጀቶች በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራምነው ያረጋገጡት፡፡

ዩሮ ፋይተር ታይፉንስ እስከ አውሮፓውኑ 2007 ድረስ በስፋት በውጊያ ይውሉ የነበሩትንና ቶርናዶፍሊት የተሰኙትን ጀቶች በመተካት ነው በስራ ላይ የሚገኙት፡፡

የአሁኑን ስምምነት ተከትሎ ኳታር የታፉን ጀቶችን ከኩባንያው በመግዛት ዘጠነናዋ ሀገር መሆን ችላለች ኳታር፡፡

በአውሮፓውያኑ 1999 የተመሰረተው የብሪታንያ የመከላከያና የኤሮስፔስ ኩባንያ፥ በተለይ ለአየር ላይ ውጊያ የሚያገለግሉ እጅግ ውድ የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ በዓለም ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን፥ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገራትን ጨምሮ ለበርካታ ሀገራት የጦር መሳሪያዎችን እያቀረበ ይገኛል፡፡/ቢቢሲ/