የዓለም አገራት ከፍልስጤም ጎን ሊቆሙ ይገባል -ፕሬዚደንት ሬሲፕ ኤርዶጋን

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን የዓለም ሀገራት ከፊሊስጤም ጎን ሊቆሙ  እንደሚገባ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በእስላማዊ ትብብር ድርጅት የጋራ ምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር እየሩሳሌም የተወረረች የፊሊስጤም መዲና ናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ናት በሚል ያስተላለፉት ውሳኔ አሁንም ማወዛገቡን ቀጥሏል፡፡

ውሳኔውን የተቃወሙት የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በኢስታምቡል እየተካሄደ ባለው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት የጋራ ምክክር  ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ሆኖዋል፡፡

የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሊ ደግሞ የአረብ ሀገራት በኢየሩሳሌም ጉዳይ ላይ ችላ ባይነትን አሳይተዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ሀገራቱ በአሜሪካ ላይ ጥገኛ የሆኑም መስለዋል ሲሉም ወርፈዋቸዋል፡፡  

የእስላማዊ ትብብር ድርጅት የጋራ ምክክር  በኢስታምቡል ከመካሄዱ አስቀድሞ ካቩሶጉሊ እንዲህ ሲሉ ተደመጡ፡፡ በስብሰባው እስካሁንም ከፊሊስጤም ጎን ለመቆም ድምጻቸውን ላላሰሙ ሀገራት ጥሪያችንን እናሰማለን ብለዋል ፡፡

 

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬስፕ ታይፕ ኤርዶጋን በስብሰባው ላይ እንዳሉት ከሆነ አሜሪካ በእየሩሳሌም ላይ ያስተላለፈችው ውሳኔ ከንቱ ጩኸት ነው፡፡  እስራኤልን የሽብር ሀገር ሲሉ ገልጸዋታል፡፡ እናም የሙስሊሙ ሀገራት በጋራ በመቆም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢየሩሳሌም ላይ ያስተላለፉትን ውሳኔ መቃወም አለብን ብለዋል፡፡ ሀገራቸው ውሳኔውን ለማስቀየር የቻለችውን ሁሉ ከመስራት ወደ ኋላ እንደማትል ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ በሰላም አደራዳሪነትዋ ይሰጣት የነበረውን ቦታ ለመንፈግ በቃች ያሉት ደግሞ የፍልስጤሙ መሪ ሞሃሙድ አባስ ናቸው፡፡ አሁን ዋሽንግተን ለእስራኤል ሙሉ በሙሉ የምታደላ ስለመሆኗ ስላረጋገጥን ሀገሪቱ ያለችበትን የትኛውንም የሰላም ድርድር አንቀበልም ብለዋል፡፡

ኢራን ፊሊስጤምን ለመደገፍ ድምፃቸውን ካሰሙ የአረቡ ሀገራት ውስጥ በቀደምትነት ልትጠቀስ ችላለች፡፡ የቴሄራን የውጭ ተልዕኮ ኮማንደር ቃሲም ሶሌማኒ እንደ ተናገሩት ኢራን በፊሊስጤም የእስላማዊ ኃይል ንቅናቄን በሙሉ አቅሟ ለመደገፍ ዝግጁ ነች፡፡ የኢራን ፓርላማ በበኩሉ የሙስሊም ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የምጣኔ ሀብት ትስስር እንዲቀኒሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከሁለት ቀናት በፊት በአከባቢው ጉብኝት አድርገው የነበሩ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ከቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ጋር በመምከር አሜሪካ በኢየሩሳሌም ላይ ያስተላለፈችውን ውሳኔ አጣጥለዋል፡፡

የፍልስጤም  ነጻ አውጪ ድርጅት መሪ ሃናን አሽራዊ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት አሜሪካ በቀጠናው ሊቀሰቀስ ስለሚችለው የፀጥታ ችግር ትኩረት አልሠጠችውም ብለዋል፡፡ እናም እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ናት የሚል ውሳኔን ማስተላለፏ ለማንም የማይጠቅም ነው ብሏል ሃናን፡፡

የሊባኖሱ ሄዝቦላ በበኩሉ አሁን ትኩረታችንን ሰብስበን በጋራ ከፊሊስጤም ጎን የሚንቆምበት ወቅት ላይ እንገኛል በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ለአሜሪካ ውሳኔ ድጋፍ ለማሰባሰብ ባሳለፍነው እሁድ ወደ አውሮፓ ያቀኑ ሲሆን በቆይታቸው ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞግሄሪኒ ጋር መክረዋል፡፡ ኔታኒያሁ በውይይታቸው የአሜሪካን ውሳኔ ትክክለኛነት በማንሳት ህብረቱ ከእስራኤል ጎን እንዲቆም ቢጠይቁም ይሁንታን አላገኙም፡፡

የአሜሪካ ውሳኔው ይባስ ብሎም በጀርመን አመፅን ቀስቅሷል፡፡ በበርሊን ጎዳናዎች የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ በመቃወም ሰልፈኞቹ የትራምፕ ፎቶዎችን እና የእስራኤል ባንዲራዎችን ሲያቃጥሉ ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን የጀርመን ባለስልጣናት የእስራኤልን ባንዲራ የማቃጠሉን ስራ በመቃወም የመንግስታቸው አቋምም እንዳልሆነ አሳውቀዋል፡፡

የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ ትችት እና ተቃውሞ ሰልፎችን በየቦታ ማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡

የእየሩሳሌም ዋና ከተማነት ጉዳይ ሁሌም በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መሃል ጠብ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሲሆን ከርሟል፡፡ ከተማዋ የእስልምና፣ ክርስትና እና ጀውሽ ሀይማኖቶች ቅድስት ስፍራ መሆኗ ደግሞ ለጠረጰዛ ዙሪያ ድርድር የማትመች አድርጎአት ቆይቷል፡፡