የሩሲያ ዋነኛ የተቃዋሚ መሪ አሌክስ ናቫሊ ከእስር ተለቀዋል

የሩሲያ ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫሊ በሀገሪቱ መጋቢት ወር ላይ የሚካሄደውን ፕሬዚደንታዊ  ምርጫ  በመቃወም በሞስኮ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ተሳትፈዋል በሚል በፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከቀናት በኋላ መፈታታቸው ተነግሯል፡፡

ዜጎችን ለአመጽ በማነሳሳት ክስ ተጠርጥረው ዘብጥያ ወርደው የነበሩት ናቫሊ ከእስር ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል እንደሚችሉም ነው የተዘገበው፡፡

የናቫሊ ጠበቃ ኦልጋ ማኪኤሎቫ ለሮይተርስ እንደተናገረችው ደንበኛዋ ያለምንም ክስ በነጻ የተለቀቁ ቢሆንም በቀጣይ ቀናት ግን ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው ተነግሮአቸዋል ብላለች፡፡

ፍርድ ቤቱ ሰልፎችን በማነሳሳት ወንጀል ከሷዋቸው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 30 ቀናት የሚዘልቅ የእስር ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ነው የተነገረው፡፡

በተጨማሪም ናቫሊም በቲውተር ገጻቸው ላይ እንደጻፉት ፍርድ ቤቱ ክሱን እስከሚያሰማበት ቀን ድረስ ከእስር ቤት መለቀቃቸውን ቢያረጋግጡም በክሱ ዙሪያ ላይ ተጨማሪ ዝርዝር ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል ነው የተባለው፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን የሀገራቸውን ዜጎች የመጋቢቱን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተቃውመው ወደ ጎዳና እንዲወጡ ጥሪ ሲያቀርቡ ታይተዋል፡፡

ተቃውሞዎችን ሲያስተባብሩ የነበሩት ናቫሊ ተቃውሞው ሲካሄድበት በነበረበት ባንዱ ቦታ በተገኙበት ወቅት የአድማ በታኝ ፖሊሶች በቀረጻ ላይ የነበሩ የቴሌቪዥን ካሜራዎች ፊት ለፊት በመግባት ከከበቡአቸው በኋላ ወደ አንድ የጭነት መኪና ውስጥ አስረው ሲያስገቧቸውት መታየታቸው የአደባባይ ሚስጥር ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡

የናቫሊ መታሰር ግን ደጋፊዎቻቸውን ተቃውሞአቸውን ከማሰማት  አልበገራቸውም ፤ይልቁንም በሞስኮ ጎዳናዎች ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የሚያጣጥሉ መጣጥፎችን ይዘው መፈክር ሲያሰሙ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ አመጽ አካሂደዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ 240  በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው ገለልተኛ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት ናቫሊ በመጋቢት 18 በሚካሄደው የፕሬዝዳንትነት ምርጫ ላይ በማጭበርበር ወንጀል በመከሰሳቸው እንዳይሳተፉ ታግደዋልም ነው የተባለው፡፡ 

ይሁንና የናቫሊ ደጋፊዎች  ክሱ ሆን ተብሎ እጩ ተወዳዳሪ  እንዳይሆኑ ለማስቻል ፖለቲካዊ ሴራን ያነገበ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በሌላ በኩል  የክሬምሊን ቤተመንግስት ተቃውሞውን "ህገወጥ" በሚል  ፈርጆ ናቫሊ ከምርጫው በፊት አለመረጋጋት ለመፍጠር ሙከራ እያደረጉ ነው ሲል ይከሳል፡፡

ሩሲያን እያስተዳደሯት የሚገኙት  ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በምርጫ ውድድሩ እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው እጩ ተወዳዳሪዎች በላቀ መልኩ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ድምጽ እንደሚያገኙና ለ4ኛ ጊዜ ሊመረጡ እንደሚችሉ ብዙዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

የፕሬዝዳንት ፑቲን ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የላቀ ግምት አግኝተው የነበሩት ናቫሊ በፈረንጆቹ 2011/12 የክረምት ወቅት የጎዳና ላይ ተቃውሞዎችን ሲያነሳሱ እንደነበር የተነገረ ሲሆን በፈረንጆቹ 2017 አመት ብቻ እውቅና ያልተሰጠውን ጸረ ፑቲን አመጽ አነሳስተዋል በሚል 3 ጊዜ ለእስር ተዳርገዋል፡፡/ቢቢሲና ሲጂቲኤን ዘግበውታል፡፡