ታሊባን ዛሬም 70 በመቶ በሚሆነው የአፍጋኒስታን ግዛቶች ውስጥ ስጋት ነው

ታሊባን አሁንም ድረስ 70 በመቶ በሚሆነው የአፍጋኒስታን ግዛቶች ውስጥ ስጋት መሆኑን ቢቢሲ ለተከታታይ አምስት ወራት በስፍራው ባከናወነው ምርመራ አረጋገጧል፡፡

ቢቢሲ ከወርሃ ነሃሴ እስከ ህዳር 2017 ዓ.ም በአፍጋኒስታን ባደረገው የምርመራ ጋዜጠኝነት በአሜሪካ የሚመራው ወታደራዊ ኃይል የታሊባን ተዋጊዎችን ለማጥፋት ሲል በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን እንዲሁ በከንቱ ማፍሰሱን ያነሳል፡፡

ምክኒያቱ ደግሞ አሜሪካ እና አጋሮቿ ታሊባንን ከአፍጋኒስታን ለማጥፋት ዘመቻ ከጀመሩ ከ17 አመታት በኃላ የታሊባን ተዋጊዎች በቀጠናው እንደ ልባቸው  ከመንቀሳቀስም አልፈው 70 በመቶ ለሚሆኑት አፍጋኒስታውያን ስጋት ሆነዋልና ነው፡፡

ቢቢሲ በመላው ሀገሪቱ ባደረገው ምርመራ የውጭ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከአፍጋኒስታን ምድር በ2014 መውጣት ከጀመሩ በኋላ ታሊባን በቀጠናው እየፈጠረ ያለው ስጋት እያየለና በቁጥጥሩ ስር እያስገባቸው የመጣው ቦታዎች ስለመበራከታቸው ማረጋገጡን ነው የዘገበው፡፡

የአፍጋን መንግስት ግን ዘገባውን በማጣጣል አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በቁጥጥሩ ስር እንደሚገኝ ያወሳል፡፡

የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋሃኒ ቃላቀባይ ሻህ ሁሴን ሙርታዛቪ በዚህ ዓመት በርካታ ስፍራዎችን ከአይ ኤስና ታሊባን የሽብር ቡዲኖች መከለላቸውን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ እንኳን በመዲናዋ ካቡል እና ሌሎች ቦታዎች በታሊባን እና የኢስላሚክ ስቴት ሚሊሻዎች የደረሱ ጥቃቶች ግን ከካቡሉ መንግስት ይልቅ የቢቢሲን መረጃ የሚያጠናክር ይመስላል፡፡

ከዓመት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ወታደር ላልተወሰኑ ጊዜያት በሀገሪቱ እንደሚቆይ ይፋ አድርገው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 3 ሺህ ወታደሮችን ወደ ስፍራው በመላክ የአሜሪካን ወታደራዊ ሃይል ወደ 14 ሺህ ከፍ ለማድረግ ሃሳብ እንዳላቸው ይፋ ማድረጋቸውም ይታወሳል፡፡

የቢቢሲ ዘጋቢዎች ጥምረት በመላ ሀገሪቱ 399 ወረዳዎችን በመዘዋወር ከ1ሺህ 200 በላይ ግለሰቦችን አነጋግረዋል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ወታደራዊ ጥቃቶችን አስመልክቶም ተነጻጻሪ መረጃዎቸን ሰብስበዋል፡፡

የጥናቱ ውጤት እንደ ሚያመላክተው 15 ሚሊዮን ህዝብ ታሊባን በሚኖርበት ወይም ቡድኑ በግልጽ ባለበትና መደበኛ ጥቃቶች በሚፈጽምበት አካባቢ የሚኖሩ ናቸው፡፡

ይህ ማለት ደግሞ ግማሹ የሀገሪቱ ዜጎች በቡድኑ ይዞታ ውሰጥ ይገኛሉ ማለት ነው፡፡

ከ2014 ጀምሮ እንኳን ሳንግን፣ ሙሳቃላ እና ናዴአሊን የመሳሰሉ የሄልማንድ ግዛት በታሊባን ስር ከወደቁ ስፍራዎች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ስፍራዎች አሜሪካ መራሽ ጦር በ2001 ታሊባንን ከስልጣን ማስወገዱን ተከትሎ የውጭ ሃይሎች ቦታዎቹን በአፍጋኒስታን መንግስት ስር ለማስገባት ሲሉ የተዋደቁበት ነው፡፡

ለአብነት ያህል ከ2001-2014ም ከ450 በላይ የእንግሊዝ ወታደሮች በዚሁ ስፍራ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በተጨማሪም አይ ኤስ ምንም እንኳን በአፍጋኒስታን ያለው ኃይል ከታሊባን ጋር ባይነጻጸርም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በስፍራው ስለመነቃቃቱ ግን የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች አስቀምጠዋል፡፡

የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በታሊባን ቁጥጥር ስር የገቡ ስፍራዎችን በሚስጥር ማቆየት በመፈለጉ ቡድኑ የተቆጣጠራቸው አከባቢዎች ብዛት አጨቃጫቂ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

ቢቢሲ በጥናቱ ወቅት ከታሊባን ነጻ ሆኖ ያገኛቸው ስፍራዎች 30 ከመቶው የሀገሪቱን ክፍል ብቻ ነው፡፡

እነዚህ ስፍራዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ቢሆኑም ከአመጽ ግን ነጻ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡      ካቡል ለዚህ ትክክለኛ ምሳሌ ናት፡፡

ታሊባን በይፋ በሚኖርባቸው ግዛቶች አርሶ አደሩንም ሆነ ነጋዴውን ግብር እንዲከፍሉ ያስገድዳል፡፡

እነዚህ ሰዎች ለትምህርትና ጤና አገልግሎታቸው ሲሉም ለመንግስት ሌላ ግብር ይከፍላሉ፡፡