ሩሲያ የኑክሊየር ስምምነቶችን ግዴታ እንድታከብር አሜሪካ አስጠነቀቀች

ዋሽንግተን አዲሱን የኑክሊየር ስምምነት ግዴታዋን ባሳለፍነው ነሃሴ ወር በማሟላት ስምምነቱን ለመጠበቅ አሁን ተራው የሞስኮ ነው ሲል ነው የአሜሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ቢሮ ያስታወቀው፡፡

ሃያላኑ ሃገራት የተፈራረሙት የኑክሊየር ቅነሳ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን እና የተቀመጠለትን የኑክሊየር መጠን ጠብቆ እንዲቀርብ የቀሩት ሶስት ቀናቶች ብቻ ናቸው፡፡

ስምምነቱ ከተፈረመበት በጎሮጎሳውያኑ የቀን ቀመር ከወርሃ የካቲት 2011 ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች ማለትም አሜሪካ እና ሩሲያ የኑክሊየር መሳሪያ እንዲቀንሱ የተቀመጠላቸው የሰባት ዓመታት የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቀው በቀጣይ እሁድ ማለትም በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በየካቲት 05/2018 ነው፡፡

በስምምነቱ መሰረት ሁለቱም አካላት 700 የሚሳኤል እና ቦምብ ጣይ ኤሊኮፕተሮች፣ 1ሺህ 550 ተምዘግዛጊ ኑክሊየር እና 800 ላውንቸሮችን ከጦር መሳሪያ ካዝናቸው እንዲቀንሱ ከስምምነት ደርሶ ነበር፡፡

እንደ የአሜሪካ መንግስት ቃል አቀባይ ሂዘር ናውርት ገለጻ ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ከስድስት ወራት በፊት በስምምነቱ የተቀመጠውን የኑክሊየር መሳሪያ ቅነሳ ስምምነትን አሟልታ ተገኝታለች፡፡

ሂዘር ናውርት ሩሲያ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ በመጠቀም ስምምነቱን እንደሚታከብር እንጠብቃለን፤ ሞስኮ ይህንኑን ስምምነቱን የማክበር ፍላጎቷን በተደጋጋሚ ጊዜያት በመግለጿ እንዳናምናት የሚያረገን ምክንያት አይታየኝም ነው ያሉት፡፡   

ሁለቱ አካላት ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲያደርጉ እንደነበርም በሚቀጥለው ወር የመጨረሻውን ዙር የዶክመንት ልውውጥ እንደሚያደርጉ ነው ቃል አቀባይዋ ለመገኛኛ ብዙሃን የተናገሩት፡፡ ከዶክመንቱ ልውውጥ በኋላም ሁለቱ አካላት አንዱ የሌላውን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ እንደሚያረጋግጡም ናውርት ተማምነዋል፡፡

የዓለማቀፉ የኑክሊየር ስምምነቶች እንደሚያመላክተው በሃያላኑ የዓለም መንግስታት እየተገነባ የመጣው የኑክሊየር የጦር መሳሪያዎች የ1987ቱን ውል ሳይቀር ወደ አዘቅት የከተተ ነው ይላል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ ቀደም ሩሲያ ያልተፈቀደውን ሚሳኤል እንደአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2014 ስታበር እንዲሁም ከስምምነት ውጭ በሆነ መልኩ ከ500 እስከ 5ሺህ 500 የመሬት ሽፋን ላይ በርቀት ጥቃት መፈጸም የሚችሉትን ሚሳኤሎች ስትጠቀም ታይታለች በሚል በይፋ ስትወቅሳት ተስተውላለች፡፡

ዘ ታይምስ ባወጣው መረጃ እንዳመላከተው ደግሞ ሩሲያ ተጠቅማለች በሚል በአሜሪካ ባለስልጣናት የተጠቀሱ መሳሪያዎቹ ኤስ ኤስ ሲ-ኤክስ-8 ንም ጭምር ያካተተ ነው፡፡

እንደአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2010 በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የኑክሊየር ስምምነቶች አዲስ ጅማሮ በሚል የተፈራረሙትን ስምምነት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የማይረቡ ስምምነቶች ናቸው በሚል መሰረዛቸው ይታወቃል፡፡

ሩሲያ የወቅቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኒኩለር መሳሪያ ባለቤት ስለመሆኗ መረጃዎች ቢያመላክቱም ሀገሪቷ እስካሁንም በጉዳዩ ላይ ያላት ሃሳብ አልተገለጸም፡፡( ምንጭ: ሮይተርስና አልጀዚራ)