የሶሪያ አማፂያን በሩሲያ የጦር አውሮፕላን ላይ ጥቃት አደረሱ

የሶሪያ አማፂያን በሩሲያ የጦር አውሮፕላን ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ሩሲያ አስታወቃለች፡፡

ኤስ ዩው 25 የተባለው የሩሲያ የጦር አውሮፕላን የበሽር አል አሳድ መንግስትን በሚቃወሙ የሶሪያ አማፂያን በተሰነዘረ ጥቃት አማካኝነት ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ነው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ለሮይተርስ የገለፁት፡፡

በሰሜናዊ የኢድልብ ግዛት ላይ የሶሪያ አማፂያን በሩሲያ እና ኢራን ከሚደገፈው የበሽር አልአሳድ መንግስት ጦር ጋር ባደረጉት ፍልሚያ የሩሲያ የጦር አውሮፕላን ጥቃት ሊያደርስ ሲል ቀድመው እንዳወደሙትም ነው የተነገረው፡፡

በጥቃቱም በትንሹ ከአምስት ሰዎች በላይ መሞታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በሶሪያ የበሽር አላሳድ መንግስትን የሚቃረኑት የሶሪያ አማፂያን ሩሲያን እንደውጭ ወራሪ ሀይል ይቆጥሯታል፡፡

ከ2015 የፈረንጆቹ ዓመት ጀምሮ ሞስኮ ከአሳድ መንግስት ጎን በመሆን በሶሪያ ያደረገችው ጣልቃ ገብነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሶሪያዊያን ህልፈተ ህይወት ተጠያቂም ያደርጋታል፡፡

አሁን የሶሪያ አማፂያን የሩሲያን የጦር አውሮፕላን ማውደማቸውን ተከትሎ አሜሪካ ለዚህ አማፂ ቡድን ሚሳኤል አቀብላ ሊሆን ይችላል በሚል ምክንያት ሩሲያ እና አሜሪካ በጥርጣሬ አይን እየተያዩ ነው፡፡

አሜሪካ ግን ምንም አይነት ሚሳኤልም ሆነ መሳሪያ በሶሪያ ለታጠቀ ቡድን እንዳላቀበለች እየገለፀች ነው፡፡