ቻይና የሚሳኤል ማክሸፊያ መሳሪያ የተሳካ ሙከራ ማካሄዷን አስታወቀች

ቻይና ለሁለተኛ ጊዜ የተሳካ የሚሳኤል ማክሸፊያ መሣሪያዋን ሙከራ ማካሄዷን  አስታወቀች ።

የሚሳኤል ማክሸፊያ መሳሪያዋ ለሀገሪቱ መከላከያ ኃይል ብርታት ሊሆን የሚችል እንጂ የትኛውንም ሀገር የሚነካ አይደለም ስትልም ቻይና ገልፃለች፡፡

ቻይና አለምን እያመሳት የሚገኘውን የሚሳኤል ቴክኖሎጅን ማክሸፍ የሚችል መሣሪያዋን የተሳካ ሙከራ ማድረጓን ነው የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  የተናገሩት፡፡

ቻይና አሁን ሙከራ ያደረገችው የፀረ ሚሳኤል መሣሪያ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የቻይናን መከላከያ ኃይል የሚያጠናክር እና ራሷን ከጥቃት ለመከላከል በሚል እንጂ ማንንም ሀገር ለመጉዳትም ሆነ ለማስፈራራት ታስቦ የተሰራ አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

አሁን ላይ ቻይና በሁሉን አቀፍ መንገድ ዘመናዊ ሚሳኤሎችን እየገነባች ያለች ሀገር መሆኗ ይ ይገለጻል ፡፡

ሀገሪቱ ከዓለም ተወዳዳሪነት የማይገኝለትን ሚሳኤልም ለማምረት ጥናት እያደረገች የምትገኝ መሆኗ የተነገረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ከጠፈር ላይ ሳተላይትን መምታት የሚያስችል የባልስቲክ ሚሳኤል እና የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን በቀላሉ ማክሸፍ የሚያስችል መሳሪያዎች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ የሚሳኤል ፕሮግራሞች በፕሬዝዳንት ዠ ፒንግ ፖሊሲ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለሮይተርስ በሰጡት መረጃ መሰረት ደግሞ  አሁን ቻይና ሰርታ ለሙከራ ያበቃችው የፀረ-ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ሙከራ የተደረገው በቻይና ድንበሮች ላይ ነው፡፡

ሙከራውም የታለመለትን ግብ መቷል፣ነገር ግን ማንንም ሀገር ለማጥቃት በማሰብ አይደለም ይልቁንስ ቻይና ራሷን ለመከላከል እንዲያስችላት የተደረገ እንጂ ብለዋል፡፡

ቻይና ከቅርብ አጋሯ ሩሲያ ጋር በመሆን በተደጋጋሚ አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ በገነባችው የፀረ ሚሳኤል ግንባታ ላይ ተቃርኖዋን ስታሰማ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ይህ ግንባታ ግን የቻይናን ፀረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ምርምር በቦታው ላይ ሊያስቀረው እንደማይችል እየገለጸች ትገኛለች፡፡

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት ቻይና እና ሩሲያ በጋራ በመሆን የጋራ የፀረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ለመገንባት መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡

አሜሪካ  በደቡብ ኮሪያ የገነባችው የጸረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ግን ጠንካራ ራዳር ያለው በመሆኑ ቻይናን በመጠኑም ቢሆን ሳያስፈራት እንዳልቀረ ነው የሚነገረው፡፡ ይህ የአሜሪካ የፀረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂም ከደቡብ ኮሪያ በቀጥታ ቻይናን በርብሮ ለማየት የሚያስችል መሳሪያ የተገጠመለት በመሆኑ ለቻይና ደህንነት ስጋት እንደሚፈጥርም ነው እየተነገረ ያለው፡፡

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ግን አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ የገነባችው የፀረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ግንባታ የሰሜን ኮሪያን ኒዩክለር መርሃ ግብር ለማክሸፍ ታልሞ የተሰራ እንጂ በማንም ሀገር ደህንነት ላይ ስጋት አይፈጥርም እያሉ ነው፡፡

ቻይና የፀረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂን አተኩራ መሥራት የጀመረችው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2010 ጀምሮ ሲሆን እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ደግሞ ለሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት እና ለወታደራዊ ኃይሏ መጠናከር ወሳኝ መንገድ መሆኑ እየተገለጸ ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡