ሩሲያና እስራኤል በሶሪያ ያላቸውን ወታደራዊ ጥምረት ለማጠናከር ተስማምተዋል

ሩሲያና እስራኤል የጦርነት ቀጠና ሆና በቀጠለችው ሶሪያ ያላቸውን ወታደራዊ ጥምረት እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል፡፡

እስራኤል በሶሪያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የኢራን ወታደራዊ ሰፈር ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡

በዚህ ወቅትም አንድ የእስራኤል ወታደራዊ አውሮፕላን በሶሪያ ሀይሎች ጥቃት ደርሶበት ተከስክሷል፡፡

በሶሪያ የሚገኝ የኢራን ወታደራዊ ሀይል ሰው አልባ አውሮፕላኑን  ከሶሪያ ምድር ወደ እስራኤል ድንበር አቅራቢያ ልኳል፤ በዚህም የእስራኤልን ሉአላዊነት ተዳፍሯል በሚል የጦር ውንጀላ ነበር እስራኤል ይህንን ጥቃት የሰነዘረችው ፡፡

ከጥቃቱ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሀገራችን ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣን የትኛውንም ድርጊት አንታገስም  ብለዋል፡፡

ኔታንያሁ አያይዘውም በሉዓላዊነታችን የመጣ ሀይልን መዋጋት መብታችንም ግዴታችንም ነው ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘም ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሶሪያ  ምድር በእስራኤል እና በኢራን መካከል የነገሰውን ውጥረት ተከትሎ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ በሶሪያ ያላቸውን ወታደራዊ ጥምረት ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀጠናው አዳዲስ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ማንኛውንም አይነት እርምጃዎች ከመውሰድ መቆጠብ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት ፡፡  

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሃኒም ሀገራት አጎራባቾቻቸውን በቦንብ በማጥቃት የሚያገኙት ነገር እንዳለ ካሰቡ ስህትት እየፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡

ሮሀኒ አንድ ሀገር ሽብርተኝነትን በመፍጠር ወይም በሌሎች ሀገራት ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት  ውጤት ይገኛል ብሎ የሚያስብ ከሆነ ስህተት እየፈጠረ እንደሆነ ጠቁመው፥ የኢራን ሀይል የቀጠናውን የደህንነት ሁኔታ ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋሽንግተን  እስራኤልን በመደገፍ ለጥቃቱ ኢራንን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፥ በሶሪያ ውስጥ ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት ሊቆም እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡