የጀርመን እና የጣሊያን ፖሊሶች የአለማችንን አደገኛ የማፊያ ቡድን በቁጥጥር ስር አዋሉ

የጀርመን እና የጣሊያን ፖሊሶች በጋራ በመሆን የአለማችንን አደገኛውን የማፊያ ቡድን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቀዋል፡፡

የሀገራቱ ፖሊሶች እንዳስታወቁት የማፊያ ቡድኑ በዘረጋው መረብ በርካታ ገንዘብ እና ንብረቶችን ለመቆጣጠር የቻለ ሲሆን በተለይም መረቡን በጀርመን፣ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና አዉስራሊያ ዘርግቶ ይንቀሳቀስ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

እንደአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1861 በጣሊያን እንደተመሰረተ የሚነገርለት ይህ የማፊያ ቡድን በጣሊያንኛ ስሙም ድራንጌታ ተብሎ ይጠራል፡፡

ይህ የማፊያ ቡድን ላይ ሰፊ ጥናት ያደረገው የጣሊያን የፀረ ማፊያ ተቋም በፈረንጆቹ 2007 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የቡድኑ አመታዊ ገቢ ከ35 እስከ 40 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል፡፡

ይህም ማለት የጣሊያንን  3 ነጥብ 6 በመቶ አመታዊ በጀት እንደማለት ማለት ነው፡፡

የቡድኑ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ደግሞ የአደንዛዥ እፅ ዝውውር ሲሆን ለህገወጥ ስራው መሸፈኛ ይሆነውም ዘንድ ህጋዊ ፍቃድ አውጥቶ የተለያዩ ስራዎችንም እንደሚሰራ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህ የሽፋን ስራዎቻቸው በዓለም ዙሪያ ሲያዘዋውሩት ከነበረው አደንዛዥ እፅ በተጨማሪ የአሸባሪ ቡድኖችን የሚቀላቀሉ የሰው ኃይልም በማሸጋገር ስራ ላይም ተጠምደው እንደ ነበሩ ተገልጿል፡፡

በተለይም በኮንስትራክሽን ስራዎች በሆቴሎች እና በሱፐርማርኬት የስራ ዘርፎች ላይ በስፋት እንደሚሰተፍም ተነግሯል፡፡

ድራንጌታ የተለዩና ከ6 ሺህ የማያንሱ አባላት ያሉት ሲሆን በእነዚህም ታማኝ አባላቱ መረቡን ከጣሊያን እስከ አሜሪካ. ካናዳ እና አዉስትራሊያ ዘርግቷል፡፡

ይህን የማፊያ ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል የቡድኑ አባላት ልክ ከአንድ ጎሳ የተገኙ ያህል ራሳቸውን መቁጠራቸው ነው፡፡

ይህም ማለት የቡድኑ አባል የሆነ ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በደም ከቡድኑ ጋር የሚገናኝ ሲሆን አባል ከሆነም በኋላ የድራንጌታ ጎሳ ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡

ከብዙ አመታት ጥረት በኋላ የጣሊያን እና የጀርመን ፖሊሶች ይህን አደገኛ የማፊያ ቡድን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለዋል፡፡