በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የተነሳው ከባድ አውሎ ንፋስ በርካታ ንብረት አወደመ

ሄሪኬን ማይክል የተባለው  ጎርፍ የቀላቀለ  አውሎ ነፋስ በርካታ ንብረት ከማውደሙም በላይ  በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተሰግቷል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁኔታው አስጊ መሆኑን በመግለፅ በፍሎሪዳ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል፡፡

እሮብ እለት በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ቀድሞ ተተንብዮ የነበረ እና በርካታ ንብረት ያወደመ ሄሪከን ማይክል የተባለ አውሎ ንፋስ ተከስቶ በርካቶችን ስጋት ውስጥ ከቷል፡፡

በሰዓት 155 ማይል ማለትም 250 ኪሎ ሜትር የሚጓዘው አውሎ ንፋሱ በተለይም በሰሜን ምእራብ ፍሎሪዳ የሚገኘው የሜክሲኮ ባህር ዳርቻን ውሃ ወደ ፊሎሪዳ እንዲጎርፍ በማድረግ ግዛቲቱን በጎርፍ እያጥለቀለቀ ይገኛል፡፡

የሲቢኤስ ዘገባ እንደሚያሳው ይህው ሃይሪኬን ማይክል የተሰኘው ከባዱ አውሎ ንፋስ በግዛቲቱ ሲከሰት እ.ኤ.አ ከ1969 ወዲህ በአደገኛነቱ የታዬ የመጀመሪያው የተፈጥሮ አደጋ ክስተት ስለመሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡

አጃንስ ፍራንስ ፕረሰ የግዛቷን አስተዳዳሪ ሪክ ስኮትን አነጋግሮ እንደዘገበው ሄሪኬ ማይክል በክፍለ ዘመኑ ከምን ጊዜውም በላይ አውዳሚው እና አደገኛው አውሎ ንፋስ መሆኑ ቀድሞም የተተነበየ መሆኑን ነው የተረዳው፡፡

የፍሎሪዳ ነዋሪዎች ሊገመት የማይችል አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡

ማእበሉ እስከ 3ነጥብ 7 ሜትር ከፍ በማለት ቀሪ ቤቶችን እንደሚሸፍንም አስተዳዳሪው ተናግሯል፡፡ አሁን ላይ 43 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል፡፡

2ሺህ 500 ብሔራዊ የአደጋ ዝግጅት አባላት በስፍራው የተሰማሩ ሲሆን አሁንም ተጨማሪ 4000ዎቹ በተጠባባቂነት መዘጋጀታቸው ነው የተዘገበው፡፡ 17000 የተለያዩ መገልገያ አቅራቢዎችም መሰናዳታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ የፌዴራል የድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደር ኤጀንሲ ሃላፊ በሩክ ሎንግ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት አውሎ ንፋሱ እ.ኤ.አ ከ1851 ወዲህ ፍሎሪዳ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ አደጋ ነው፡፡

የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁኔታው አስጊ መሆኑን በመግለፅ በፍሎሪዳ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው በፌደራል ደረጃ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግም አዘዋል፡፡