ሲንጋፖር ፖሊሶች የማህበራዊ ገጾችን ይዘት ማጥፋት የሚችሉበትን ህግ ማውጣቷ እያነጋገረ ነው

ሲንጋፖር ፖሊሶች የማህበራዊ ገጾችን ይዘት ማጥፋት የሚችሉበት ህግ ማውጣቷ እያነጋገረ ነው፡፡
ሲንጋፖር የሀሰት ዜናዎችን ለመቆጣጠር ያሳለፈችው አወዛጋቢ ህግ ፖሊሶች በማህበራዊ የትስስር ገጾች እና ግለሰቦች በቡድን የሚደረጉትን የመልዕክት ልውውጦችን ሳይቀር ማጥፋት የሚያስችል ስልጣን የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡

መንግስት ‘’የህዝብን ፍላጎት ጋር ተጻራሪ የሆኑ’’ የሀሰት ዜናዎች ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ማስወገድ ወይም እርማት እንዲሰጣቸው ማዘዝ እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ቅጣቱ ዜጋውን ከሀሰተኛ ዜናዎች የሚጠብቀው ነው ሲል ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ተቺዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ህጉ በህብረተሰቡ ነጻነት ላይ ከባድ ስጋት እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም በአንዳንድ መተግበሪያዎች ላይ ማለትም ዋትስ አፕ፣ ቴሌግራምና ሌሎች ላይ ህጉ እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ ግልጽ አይደለም ይላሉ፡፡

በሲንጋፖር መንግስት የሀሰት ዜና ነው ብሎ ባመነባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ አንድ ግለሰብ በከባድ ቅጣት ወይም እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም የሀሰት አካውንቶች በመክፈትና የሀሰት ዜናዎችን በማሰራጨት ሲጠቀም የተገኘ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር እና እስከ 10 አመት የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡

ህጉ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች እስከ የዜና ዌብሳይቶች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

በዘር እና በሃይማኖት ላይ ቀውስ የሚያስከትሉ የሀሰት ዜናዎችን ለመቆጣጠር ህጉ አስፈላጊ መሆኑን የሲንጋፖር መንግስት አስታውቋል፡፡

ሲንጋፖር በቅርብ ወራት የሀሰት ዜናዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በተመለከተ ጠንካራ ህጎችን ካሳለፉ እንደ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ካሉ አገራት ጋር ተቀላቅላለች ተብሏል፡፡

ምንጭ ፡- ቢቢሲ