በሜክሲኮ የአየር ብክለት በፈጠረው ጭጋግ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

የሜክሲኮ መንግሥት በሜክሲኮ ከተማና አካባቢዋ በተፈጠረ ከፍተኛ የአየር ብክለት ምክንያት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ማተላለፉ ተገለጸ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ውሳኔው 20 ሚሊየን ህዝብ በሚኖሩባት በሜክሲኮ ከተማና አካባቢ በሚገኙ የህዝብ እና የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ ይሆናል ብሏል፡፡

ህጻናት አካላዊ እንቅስቃሴን ከማድረግ እንዲቆጠቡ እና በቤት ውስጥ እንዲቆዩም ተመክሯል፡፡

የከተማዋ ባለሥልጣናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን በብክለቱ የተፈጠረው ጭስ እና አመድ እይታን መቀነሱ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ብክለቱን "እጅግ የሚያጸጽት" ሲሉ ገልጸውታል፡፡

በአቅራቢያ ከሚቃጠል ጫካ የሚወጣው ጭስ ብክለቱን ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ ማድረጉንና ይህም ለሰው ልጆች ጤንነት አደገኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡

(ምንጭ፡-ሲ.ኤን.ኤን)