ሰሜን ኮሪያ ከባድ ድርቅ አጋጥሟታል

ሰሜን ኮሪያ በ37 ዓመት ታሪክ እጅግ ከባድ የተባለ ድርቅ እንደገጠማት ይፋ አድርጋለች። በድርቁ ምክንያትም ሰብሎች ደርቀዋል፤ ዜጎች የሚበሉትን ለማግኘትም ተቸግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው፤ አስር ሚሊየን የሚደርሱ ሰሜን ኮሪያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ በዚህ ዓመት እያንዳንዱ ሰሜን ኮሪያዊ የእለት የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት 300 ግራም ምግብ ብቻ ነው የሚያገኘው።

በአውሮፓውያኑ 1990 አካባቢ ባጋጠመ ረሃብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን ህይወታቸው አልፏል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ሀገሪቱ 1.5 ሚሊየን ቶን ምግብ ከውጪ ሀገራት ማስገባት አለባት።

በ2018 ሃገሪቱ ያመረተችው ምርትም እጅግ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።

የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ባጋጠመኝ ውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ምግብን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ወደሃገር ውስጥ ማስገባት አልቻልኩም በማለት በተደጋጋሚ አስታውቋል።

አሁን ያጋጠማት ድርቅ እጅጉን የከፋ ሲሆን፤ ብዙ ዜጎች በምግብ እጥረት ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችልም ቢቢሲ ዘግቧል።