በሕንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በተነሳ እሳት 19 ተማሪዎች ሞቱ

በሕንድ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 19 ተማሪዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

በትምህርት ቤቱ የተነሳው ቃጠሎ ተፋፍሞ ጥቁር ጭስ በመስኮቶቹ መውጣት እንደጀመረ ተማሪዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ በመስኮት ሲዘሉ መታየታቸው ተዘግቧል።

በእሳቱ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎቹ አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች ናቸው የተባለ ሲሆን፤ በትምህርት ቤቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እየወሰዱ ነበር።

እሳቱ የተነሳበት ምክንያት ባይታወቅም፤ ተማሪዎች በብዛት ወደሚገኙበት ክፍል የተዛመተው ተቀጣጣይ በሆነው ኮርኒስ ሰበብ ነው ተብሏል።

20 ተጨማሪ ተማሪዎች ከፍተኛ ጉዳት ያጋጠማቸው ሲሆን፤ በጉጅራት በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እያገኙ እንደሆነ ተገልጿል።

የአካባቢው ባለስልጣን የሆኑት ዲፓክ ሳፕታሌ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል "ተማሪዎቹ ሕይወታቸውን ያጡት በእሳቱ ምክንያትና ከእሳቱ ለማምለጥ በመስኮት በሚዘሉበት ወቅት ነው" ብለዋል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ሟቾቹ በአጠቃላይ እድሜያቸው ከ20 በታች ሲሆን፤ እሳቱ መወጣጫ ደረጃ አካባቢ በመከሰቱ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በትዊተር ገፃቸው ሐዘናቸውን ገልጸው፤ የአካባቢው ባለስልጣናት አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ በሦስት ቀን ውስጥ ውጤቱ ይፋ አንዲደረግ ታዟል። መረጃው የቢቢሲ ነው፡፡