በአሜሪካ የስደተኞች ካምፕ አያያዝ አስደንጋጭ መሆኑ ተገለጸ

በአሜሪካ የስደተኞች ካምፕ ህፃናትን ጨምሮ የስደተኞች አያያዝ እንዳስደነገጣቸው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ሃላፊ ሚሼል ባችሌት ገልፀዋል፡፡

ህፃናት ያለ በቂ ህክምና እና ምግብ በጣም በተጣበበ የስደተኞች ካምፕ መሬት ላይ እንዲተኙ መደረጉ አስደንግጦናል ነው ያሉት።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለ2020 ቅድመ ምርጫ በስደተኞች ዙርያ ያላቸው አቋም ዋና ጉዳይ መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ዴሞክራቲክ ፖለቲከኞች እና ሲቪል የመብት ተሟጋቾች በአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ስደተኞች በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት ቅዠት የሚመስል በጣም የተጨናነቀ በቂ የምግብና የውሃ አቅርቦት የሌለው ካምፕ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የአገር ውስጥ ደህንነት ዲፓርትመንቱ ዋና ተቆጣጣሪ በቴክሳስ ሪዮንግ ጉርድ ቫሊ ውስጥ የሚገኙ አጠቃላይ ስደተኞች ማቆያ ማዕከሎች በመጨናነቃቸው ሁለት ጊዜ በመሄድ ፎቶግራፎችን አንስተው ማሳተማቸው ተነስቷል፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች ከአካባቢያቸው ርቀው ለስደት የሚዳረጉት ራሳቸውን ከጦርነትና ከረሃብ ለማዳን መጠለያ ፍለጋ መሆኑን የተናገሩት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ሃላፊ፤ ደህንነት የሚሰማቸው ቦታ ቢደርሱም በጣም ከሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው መነጠላቸው ደህንነት እንዳይሰማቸውና መረጋጋት እንዳይኖራቸው የሚያደርግና ሁኔታው የትም ቢሆን ለማንም ሊያጋጥመው የማይገባ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ)