4ኛው የኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

የኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በአዲስ አበባ

ሐምሌ 24/2015 (ዋልታ) አራተኛው የኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተከሄደ ነው፡፡

በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እና በሁለቱም ወገን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ደቡብ አፍሪካ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት በፕሪቶርያ ላደረጉት ብስለት ለተሞላበት አመራር እቅውናና አክብሮት እንሰጣለን ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ትብብር እያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸው የሚኒስትሮች ጉባኤም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከፍ ወዳለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን አንስተዋል።

ጉባኤው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙት የሚያሳድጉ የመግባቢያ ስምምነቶችን ከመፈራረም በተጨማሪ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር በበኩላቸው ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተው ኢትዮጵያ በኔልሰን ማንዴላ ትግል ወቅት ያደረገችውን ድጋፍ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊና አህጉራዊ ውህደት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራች መሆኗን ገልጸው አገሪቱ እውነተኛ ፓን አፍሪካኒስት ሀገር ነች ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለአህጉራዊ ውህደትና ኢኮኖሚያዊ እድገት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በመስከረም ቸርነት