ከሀገራችን ወጪ ንግድ ከ2ነጥብ 86 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ ፡፡

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 29/2008 (ዋኢማ) የንግድ ሚኒስቴር ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 86 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ4ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ 2 ቢሊየን 86 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሆኗል ፡፡

በወጪ ንግዱ ግብርና ከ75 በመቶ በላይ ፣ማኑፋክቸሪንግ ከ12 በመቶ በላይ ፣ማዕድን ከ10 ነጥብ8  በመቶ በላይ እና ሌሎች ከ1ነጥብ6 በመቶ በላይ ድርሻ እንደነበራቸው ጠቁመዋል፡፡

ይህ አፈጻጸም ከባለፈው በጀት ዓመት ከተገኘው 2ቢሊየን 99 ቢሊዮን ዶላር ሲነጻጸር ከ139ሚሊየን ዶላር በላይ ማለትም 4ነጥብ 65 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አመልክተዋል ፡፡

የዚሁ ምክንያትም ወደ ውጭ ከተላኩት ውስጥ የላቀ ድርሻ ያለው የግብርና ምርት በመጠን የተሻለ አፈጻጸም ቢኖሮውም ፤ በዓለም ገበያ መውረድ ምክንያት የሚፈለገው ገቢ ሊገኝ ባለመቻሉ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

እንደዚሁም ወደ ውጭ የሚላኩት ምርቶች ተከታታይነት ጥራት ያላቸው ሆነው ወደ ዓለም ገበያ ባለመቅረባቸው መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

ችግሩ ለመፍታትም መኒስቴሩ የሀገራችን ወጪ ንግድ ምርቶች በጥራት ፣በተወዳዳሪ ዋጋና በሚፈለገው መጠን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል ፡፡

የሀገራችን የወጪ ምርቶች ገቢያ መዳረሻዎች አንደኛ ኤስያ ፣ሁለተኛ አውሮፓና ሶስተኛ አፍሪካ አገሮች መሆናቸውን ከአቶ አሰፋ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡