ከ39 ሺህ በላይ የጋራ መኖርያ ቤቶች በዕጣ ለዕድለኞች ተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2008 (ዋኢማ)- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ39 ሺህ በላይ የጋራ መኖርያ ቤቶች ዛሬ ለተጠቃሚዎች በዕጣ ተላለፉ።

በዕጣ የተላፉት ቤቶች በ10/90 እና በ20/80 የቤቶች መርሀ ግብር ተመዝግበው ሲጠባበቁ ለነበሩ ዜጎች ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ 23 ሺህ 16 የሚሆኑት ለ10/90 ተመዝጋቢዎች፤ 14 ሺህ 516 የሚሆኑት ደግሞ ለ20/80 ተመዝጋቢዎች ተላልፈዋል፡፡

ቤቶቹ ለዕድለኞች መተላለፋቸው መንግስት በከተማዋ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን የቤት ችግር በየጊዜው ለመፍታት እየተከተለ ያለው ልማታዊ አቅጣጫ አንዱ አካል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናረዋል፡፡

መንግስት የቤት እጥረት ችግርን ለመፍታት ባለፉት አስር ዓመታት ከ136ሺ በላይ ቤቶችን ገንብቶ ለዕድለኞች በዕጣ ማስተላለፉን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድርጓል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ከ60ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ከንቲባው አስታውሰዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደረጁ ወጣቶችና ሴቶች ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አስረድተዋል፡፡

ለ11ኛ ዙር የቤቶች ልማት ግንባታ ለቤቶች ግንባታና ለመሰረተ ልማት 17 ቢሊዮን ብር ወጭ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ የሚተላለፉበት ዋጋም በ10ኛው ዙር ከነበረው ተመሳሳይ እንደሆነ ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም ከ130ሺ በላይ ቤቶች በግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል-ከንቲባው፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጄንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ በበኩላቸው በእጣው ተሳታፊ የሚሆኑት 29 ወር በትክክል የቆጠቡና ተከታታይ ስድስት ወራት ቁጠባቸውን ያላቋረጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው እንዳሉት ከ10/90 ተመዝጋቢዎች መካከል ቁጠባቸውን ካቋረጡ 2 ሺህ 111 ተመዝጋቢዎች በስተቀር ሁሉም በእጣው ይካተታሉ። ከሚተላለፉት ቤቶች በተጨማሪ 1 ሺህ 717 የንግድ ቤቶችም ተገንብተው ተዘጋጅተዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በቦሌ፣አቃቂና በልደታ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ መሆናቸውን ተናረዋል፡፡ በዕጣው የተካተቱት ለ29 ወራት የቆጠቡ ናቸው ብለዋል፡፡ 

ዛሬ እጣ የሚወጣባቸው ቤቶች በቂሊንጦ፣ በልደታ ቦሌ አራብሳ፣ በቂርቆስ ቦሌ አራብሳ እና በኮዬ ፈጬ፣ ልደታ መልሶ ማልማት፣ በፕሮጀክት 15 ቦሌ አራብሳ፣ በቦሌ አያት 3፣ 4 እና 5 የተገነቡ ናቸው።

መንግስት የመሰረተ ልማት ወጪዎችን የውሃ፣ የመብራት እና የፍሳሽ መስመሮችን እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የግንባታ እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ በማድረግና በሌሎችም መንገዶች ድጋፍ በማድረግ እንደተሰሩ ተመልክቷል።

በ10/90 መርሃ ግብር 23 ሺህ 016 ቤቶች ዕጣ የሚወጣባቸው ሲሆኑ፥ ቤቶቹን ለማግኘት እየቆጠቡ ያሉት 19 ሺህ 342 ተመዝጋቢዎች ባለቤት ይሆናሉ።

ከዕጣው የሚተርፉት ከ3 ሺህ በላይ ቤቶች በኪራይ ወይም አስተዳደሩ በሚወስነው መሠረት እንደሚተላለፉም ነው የተመለከተው።

በ20/80 መርሃ ግብር የተገነቡ 14 ሺህ 516 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለዕጣ ዝግጁ ተደርገዋል። ከእነዚህ ውስጥ በቦሌ አያት 3፣ 4 እና 5 የሚገኙ 1 ሺህ 657 ቤቶች ለልማት ተነሺዎች ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡

ቤቶቹ በተገነቡባቸው አካባቢዎች 46 መዋእለ ህጻናት፣ 14 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ስድስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና አራት የጤና ጣቢያዎች ግንባታቸው እየተጠናቀቁ መሆኑም ተገልጿል።

የ72 ኪሎ ሜትር የመንገድ ስራ መጠናቀቁንና 89 የጋራ መገልገያ ህንጻዎች ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውም ተጠቁሟል።