በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 148 ሺ 227 ነጥብ 2 ቶን ቡና ፣ቅመማ ቅመምና ከሻይ ቅጠል ምርቶች ወደ የተለያዩ አገራት ተልከው 560 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳኒሶ እንደተናገሩት ባለስልጣኑ 170 ሺ 354 ነጥብ 72 ቶን በመላክ 649 ሚሊየን ዶላር ለማግኝት አቅዶ ነበር፡፡
ባለስልጣኑ ካቀደው በመጠን 85.55 በመቶው ከገቢ ደግሞ 86.3 በመቶውን ማሳካት ችሏል፡፡
አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 4.5% በገቢ 15% ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል፡፡
ወደ ውጭ ከተላከ 139 ሺ 887 ቶን የቡና ምርት ብቻ 545 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ የእቅዱን በመጠን 88.12 % ና በገቢ 87.91 % መሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ 241 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 941 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር አቅዶ እየሰራ መሆኑም ታውቋል፡፡
በቀሪዎቹ ሶስት ወራት የቡና ምርት ለገበያ የተሻለ የሚቀርብበት በመሆኑ የዓመቱን እቅድ ለማሳካት እንደሚቻልም ተመላክቷል ( ኢዜአ)