ባንኩ የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማረጋጋት የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ ዝውውርን መግታት አለበት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቷን የፋይናንስ ስርዓት ለማረጋጋት የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ ዝውውርን መግታት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንኩን የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሲመረምር እንዳለው ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ ስርጭትን ሊከታተልና ሊቆጣጠር ይገባል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ አበበ "የአገሪቱን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የውጭ  ምንዛሪ የጥቁር ገበያው ዕንቅፋት ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል ባንኩ ከመንግስት ግዥ ጋር ያለመናበብ፣ ከዕቅድ በታች የኦዲት ክንውንና የሰው ኃይል ፍልሰት ምክንያቶችን አጥንቶ ምቹ ሁኔታ ያለመፍጠር ውስንነቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል።

ክፍተቶቹን መድፈን፣ ችግሮቹን መፍታትና መልካም አስተዳደር ማስፈንን የቀጣይ ሩብ ዓመት ሥራዎቹ እንዲያደርግም አሳስቧል።

ተደራሽነቱን ለማስፋት ቅርንጫፎቹን በማስፋት ያከናወናቸውን ተግባራት በጥንካሬ አንስቷል ቋሚ ኮሚቴው።

የብሔራዊ ባንክ አዛዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በውጭ ምንዛሪ የሚከናወነው ጥቁር ገበያ ውስብስብና ከባድ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመ ግብረ ኃይል ንዑስ ኮሚቴ መዋቀሩን ጠቁመው ባንኩ በጋራ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በግብረ ኃይሉ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ጥናት እያካሄዱ መሆኑንና ጥናቱ ተጠናቆ ሲፀድቅም ወደ ስራ እንደሚገባ አክለዋል።

የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠርና ለማዳከም ዋናው መፍትሔ ግን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦትን ማመጣጠን መሆን አለበት ብለዋል።

የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገው ሽግግር መፋጠን እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።

በአገሪቷ እየተካሄዱ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታዎች አንድ የመፍትሔ አካል መሆናቸውን አስታውሰዋል።( ኢዜአ)