የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘንድሮ የበጀት ዓመት 14 ቢሊዮን ብር ብድር ለመሥጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ ።
የባንኩ ስትራቴጂክ ለውጥና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ኃይለየሱስ ለዋሚኮ እንደገለጹት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባንኩ በፕሮጀክቶች ብድርና በሊዝ ፋይናንሲንግ የብድር ሥርዓቱ በአጠቃላይ የ14ነጥብ 03 ቢሊዮን ብር ብድርን በማጽደቅ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ተዘጋጅቷል ።
ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት በአጠቃላይ 12 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር ብድር መሥጠቱን ያስታወሱት አቶ ክፍሌ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባንኩ የሚሠጠውን የብድር መጠን ወደ 14 ነጥብ 0 3 ቢሊዮን ብር ማሳደጉን ተናግረዋል ።
በዘንድሮ ዓመት ባንኩ በአገሪቱ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሽግግርን ሊያፋጥኑ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ለሚሠማሩ ፕሮጀክቶችና ኢንተርፕራይዞች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራ አቶ ክፍሌ አመልክተዋል ።
መንግሥት የአገሪቱን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ድጋፍ ለማድረግ ባስቀመጠው የልማት አቅጣጫ መሠረት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባንኩ በዘረጋው የሊዝ ፋይናንስ ብድር ሥርዓት መሠረት በአጠቃላይ ለማሽነሪ ግዠ 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ለመፍቀድ መዘጋጀቱን አቶ ክፍሌ ተናግረዋል ።
እንደ አቶ ክፍሌ ገለጻ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባንኩ ከተበዳሪዎች 5ነጥብ 67 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱንና አጠቃላይ የባንኩን የብድር መጠን ወደ 40 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ።
ባንኩ በዘረጋው የሊዝ ፋይናንስ አሠራር ከፕሮጀክት አነስ የሚሉና በአነስተኛና ቁጠባ ተቋማት መስተናገድ የማይችሉ አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ኢንተርፕራዞች ከ1ነጥብ5 እስከ 30 ሚሊዮን ብር ብድር እየሠጠ መሆኑ ተመልክቷል ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2009 የበጀት ዓመት ከፕሮቪዥንና ከታክስ በኋላ የ323.85 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ይታወሳል ።