ኡጋንዳና ሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ለማጠናከር እንደሚሠሩ ገለጹ

ኡጋንዳና ሱዳን የሁለትዮሽ  ግንኙነታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑካን ከአንድ ወር በፊት በኡጋንዳ ለሁለት ቀናት ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡

በወቅቱ የኡጋንዳያው አምባሳደር ፓትሪክ ሙጋያ ሀገራቱ በካርቱም በተደረገው አምስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ካርቱም በተካሄደው ውይይት በንግድ እና ኢንቨስትመንት፤ በኢሚግሬሽን፤ በአየር ትራንስፖርት፤ በአህጉራዊ ጉዳዮች እና በደህንነት አጀንዳዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በፈረንጆቹ መስከረም 2015 በሱዳን የሁለት ቀናት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በወቅቱም ለትምህርት ባለሙያዎችና ለሲቪል ማህበረሰብ አካላት በምጣኔ ሃብታዊ ልማት እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ 

ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ በፈረንጆቹ ታህሳስ 2016 ለሁለተኛ ጊዜ በካርቱም በመገኘት ከሱዳኑ አቻቸው ጋር የሀገራቱን ግንኝነት የበለጠ ለማጠናከር በሚያችላቸው ጉዳይ ዙርያ መክረዋል፡፡

ሱዳን ከኡጋንዳ የቡና ምርት 20 በመቶውን ወደ ሀገሯ የምታስገባ ሲሆን 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ታደርጋለች፡፡  በዓለም የቡና ገበያም ትልቅ ድርሻ እንዳላት ይነገራል፡፡

ከሱዳን የደረጃዎች እና የሥነ-ልክ ባለሞያዎች የተውጣጡ ልዑካን የኡጋንዳን የቡና ልማት ኤጀንሲ ጥራት ለማረጋገጥ ከሰባት ቀናት በፊት ወደ ካምፓላ አቅንተዋል፡፡ በቆይታቸውም ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቡና ግብይት ዙሪያ መክረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አል በሺር እ.ኤ.አ በህዳር 12/ 2017 በሚያደርጉት ጉብኝት ከንግድ ሚኒስትር፤ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከተለያየ አካላት  ከተዉጣጡ ልዑካን ጋር ወደ ስፍራው ያቀናሉ ነው የተባለው ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ሁለቱ ሀገራት የንግድ ፎረም እንደሚያካሄዱ ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይ ኡጋንዳ የሁለቱን ሀገራት ስድስተኛውን የጋራ ኮሚሽን ጉባኤ በመጪው 2018 የፈረንጆቹ ዓመት እንደምታስተናግድ ታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት አልበሽር ወደ ካምፓላ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት መጠናቀቅ ተከትሎ ከኡጋንዳ አቻቸው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በመሆን  መግለጫ እንደሚያወጡ ከወዲሁ ይጠበቃል ። ( ምንጭ:ኒውስ ናው)