የታንዛኒያ ሴቶች ባንክ ለ86ሺህ ታንዛንያውያን ሴቶች ከ120 ቢሊዮን ሺሊንግ በላይ ብድር ማሠራጨቱን አስታወቀ

አንድ የታንዛንያ ሴቶች ባንክ ለ86 ሺህ ታንዛኒያዊያን ሴቶች ከ120 ቢሊዮን ሺልንግ በላይ በብድር ማሠራጨቱን  ገለጸ፡፡

በሃገሪቱ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ታንዛኒያዊያን የሴቶቹ ተሳትፎ 30 ከመቶ ብቻ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ከሃገሪቱ ብሔራዊ ማይክሮ ፋይናንስ ባንክ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከ7 ነጥብ 5 ከመቶ በላይ ታንዛኒያዊያን የሂሳብ ደብተር በመክፈት የባንክ ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሴቶቹ ቁጥር ከ30 በመቶ የሚበልጥ አይደለም፡፡

ይህን የሴቶች የመቆጠብ ባህል አነስተኛ መሆን ያሳሰበው የታንዛኒያ የሴቶች ባንክ የሃገሪቱ ሴቶች በባንክ የሚጠቀሙ ሴቶችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የታንዛኒያ ሴቶች ባንክ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለታንዛኒያዊያን ሴቶች በብድር እየሰጠ ነው፡፡

ባንኩ ከፈረንጆች 2007 አንስቶ ባለፉት አሥር አመታት ውስጥ ለ86 ሺህ ሴቶች ከ120 ቢሊዮን የታንዛኒያ ሺልንግ በላይ በብድር አሠራጭቷል ነው የተባለው፡፡   

የታንዛኒያ ብሄራዊ ማይክሮ ፋይናንስ ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኤነኬ ቡዝማከር ሴቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሰማራት የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚነታቸውን እና የቁጠባ ባህላቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ንግግራቸውን ሲቀጥሉም ከዚህ ቀደም የነበሩ አንዳንድ የባንክ አሠራሮችን በመቀየር እና ለሴቶች ምቹና ቀልጣፋ የብድር አገልግሎት በማመቻቸት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የታንዛኒያ ሴቶች ባንክም ለሴቶቹ ያሠራጨችው ከፍተኛ ገንዘብም የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ነው የጠቆሙት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፡፡ በዚህም የበርካታ ታንዛኒያዊያን ሴቶችን የባንክ ተጠቃሚነት ማሳዳግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በመላው ዓለም ከሚገኙ እንስቶች መካከል ወደ አንድ ቢሊዮን የሚሆኑት ሴቶች ፈጽሞ በባንክ የመጠቀም ልምድ እንደሌላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ ፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሃገራት የሴቶችን የባንክ ተጠቃሚነትና ትርፋማነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት የህንድ፣ ሜክሲኮ፣ ግብጽና ናይጄሪያ ሴቶች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የዓለም ሴቶች ባንክ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡