የአፍሪካ ህጻናትን የድህንት ምጣኔ ለመቀነስ መንግሥታት ያወጧቸውን ፖሊሲዎች ሊተገብሩ ይገባል

በአፍሪካ የህጻናትን የድህነት ምጣኔ ለመቀነስ መንግሥታት ያወጧቸውን ፓሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በትክክል ተግባራዊ  ማድረግ እንደሚገባቸው የአፍሪካ የህጻናት ፖሊሲ ፎረም የዓለም አቀፍ ቦርድ አስታወቀ ።

በአፍሪካ የህፃናትን የድህነት ምጣኔ ለመቀነስ "ቅድሚያ ለህፃናት" በሚል መሪ ሐሳብ አለም አቀፍ ጉባኤ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ እየተካሄደ ሲሆን እኤአ በ2016 ይፋ የሆነው የአፍሪካ ህፃናት ደህንነት ሪፖርት እንደሚያሳየው በአፍሪካ የህፃናት አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በቀን ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ዶላር በታች ነው።

ከ34 ሚሊዮን የሚበልጡ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 54 በመቶ  የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ በአህጉሪቷ ከሚገኙ ህፃናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በህፃንነታቸው ለህልፈት የሚዳርጋቸውን የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት አያገኙም ብሏል፡፡

በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የተቀመጡትን እቅዶች በማሳካት ህፃናትን ከተደቀነባቸው ችግር ለማውጣት "የአፍሪካ መንግስታት ያወጧቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በትክክል መተግበር አለባቸው" ተብሏል።