የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዛምቢያ አየር መንገድን 45 በመቶ ድርሻ ሊገዛ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ እንደ አዲስ በይፋ ስራ የሚጀምረውን የዛምቢያ አየር መንገድ 45 በመቶ ድርሻ ሊገዛ መሆኑ ተገለፀ።

የዛምቢያ ተጠባባቂ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ስቴፈን ኮምፖዮንጎ አዲስ በሚቋቋመው የዛምቢያ አየር መንገድ ውስጥ ሀገሪቱ 55 በመቶ ድርሻ ሲኖራት፥ ቀሪውን የአየር መንገዱ 45 በመቶ ድርሻ  ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚይዘው ነው ያስታወቁት። 

ተጠባባቂ ሚኒስትሩ የዛምቢያ አየር መንገድ የመጀመሪያ ዓመት የስራ ማስጀመሪያ እና ስራ ማስኬጂያ 16 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት እንደሚያገኝም ተናግረዋል።

በዚህ ዙሪያ ከአንድ ወር በኋላ የሀገሪቱ ፓርላማ ውይይት እንደሚያካሂድበት የዘገበው ሉሳካ ታይምስ ነው፡፡