ቻይና የአንድ ቀለበት አንድ መንገድ ግንባታን ለማፋጠን ከ 86 ተቋማትና አገራት ጋር ስምምነት ፈጸመች

ቻይና ከአውሮፓ፣ እስያ እና ከአፍሪካ ጋር የሚያስተሳስራትን የአንድ ቀለበት አንድ መንገድ ግንባታን ለማፋጠን ከ86 አለም አቀፍ ተቋማት እና ሃገራት ጋር ሰሞኑን ስምምነት ማድረጓ ተገለጸ ፡፡

ከዓለም ሃገራት ጋር በንግድ ለመተሳሰር እና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ከዓለም ቀዳሚ ለመሆን እየተንቀሳቀሰች የምትገኘው ቻይና ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ያላትን ትሰስር  ለማጠናከር የአንድ ቀለበት አንድ መንገድ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግም ሰሞኑን ከ86 አካላት ጋር ስምምነት አድርጋለች፡፡

ሃገሪቷ ለትብብር መንገዱ ከፍተኛ ትኩረት በመሥጠቷ ከመቼውን ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ላይም ትገኛለች፡፡

የኢኮኖሚ እድገቷን እ.አ.አ በ2010 ከነበረው እድገት ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ማሳደግ እንዳለት የሃገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እቅድ ባለሞያዎች በዋና ከተማዋ ቤጂንግ በተዘጋጀው ዓመታዊ የጋራ ስብሰባቸው ላይ ገልፀዋል፡፡

አንድ የሃገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እቅድ ባለሙያ እንናደተናገሩት እነዚህ 86 አለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሃገራት ከቻይና ጋር በመተባበር የትብብር መንገዱን ግንባታ ለማፋጠን የሚረዱ 100 ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡

የትብብር መንገዱን ለመገንባት በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ10 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ሊያስፈል እንደሚችል ይገለፃል፡፡

የሃገሪቱ ብሔራዊ የልማት እና ሪፎርም ኮሚሽን ዋና ሃላፊ ሊፈንግ  በበኩላቸው የትብብር መንገዱ ዋናው መንገድ መሻሻሎችን እያሳየ ሲሆን በአቅም ግንባታ ፣ በኢንቬስትመንት እና በዲጅታል ጎዳናዎች እንዲሁም ቁልፍ በሆኑ ዘርፎችም በተመሳሳይ መሻሻል  እየታየበት ነው ብለዋል፡፡

ቻይና ከዓለም ሃገራት ጋር የንግድ ትስስር በመፍጠር ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት እየተፋጠነ ሲሆን የቻይና-ፓኪስታን ኢኮኖሚክ ኮሪደሪን በመገንባት ረገድም ዘላቂ እድገት  እንዳሳየ  ኃላፊው አክለው ገልጸዋል ፡፡

እ.ኤ.አ. በ 2018 የሃገሪቱ ብሔራዊ የልማት እና ሪፎርም ኮሚሽን በትብብር መንገዱ ዙሪያ የተደረጉ ለዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚያተኩር አስታውቋል፡፡ ( ምንጭ:  ሲጂቲኤን )