በሑመራ በኩል ከተላኩ የግብርና ምርቶች 65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

ባለፉት ስድስት ወራት በሑመራ በኩል ለውጭ ገበያ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ።

የሑመራ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ምሩጽ አብርሃ ለኢዜአ እንዳሉት ገቢው የተገኘው በሱዳንና በጅቡቲ ወደብ ወደተለያዩ ሀገራት ተልኮ ለገበያ ከቀረበ ሰሊጥ፣ ቅመማ ቅመም፣ ጥራጥሬና የእንስሳት ተዋጽኦ ነው።

ምርቱ ወደ አውሮፓና እስያ ሃገራት መላኩን ገልጸው፣ ለውጭ ገበያ ከቀረበው የሰብል ምርት ውስጥ 509 ሺህ ኩንታል የሚሆነው ሰሊጥ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደኮሌኔል ምሩጽ ገለጻ በግማሽ ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ምርት ሽያጭ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ16 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ አለው።

በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢዎች በተፈጠሩ ህጋዊ የንግድ ትስስሮች ቀደም ሲል በስፋት ይታይ የነበረው የኮንትሮባንድ ህገ ወጥ ንግድ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ የተሻለ ገቢ እንዲገኝ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።