በሊቢያ በስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ ኢ- ሰብዓዊ ተግባራት ዘግናኝ ነው

ከሊቢያ ወደ ሞቃዲሾ የተመለሱ የሶማሊያ ስደተኞች በሊቢያ በስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ ተግባራት ዘግናኝ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አብዱል ከሪም ሙሀመድ ኦማር 22 አመቱ ነው፡፡

አሁን ከብዙ ውጣ ውረድና ችግር በኋላ ወደሃገሩ ቢመለስም የስደት ሰቆቃን ያየበትን ጊዜ ያስታውሳል፡፡

ሊቢያ ለመድረስ በእግሩ ወደ ኢትዮጵያ ከዛም ወደ ሱዳን ያመራው ከ150 ጓደኞቹ ጋር የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ነበር፡፡

ከነዚህ ጓደኞቹ መካከል አብዛኛዎቹ በየበረሃው ወድቀው መቅረታቸውንም ያስታውሳል፡፡

ከሱዳን ወደ ሊቢያ ለመድረስ የተጫኑባት ተሸከርካሪ በረሃው በከበደው ቁጥር በየስፍራው እየቀነሰ ጥሏቸዋል፡፡

በበርካታ አለመግባባቶች ከህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር የሚፈጠር ግጭት ስደተኞችን ለከፋ የአካል ጉዳት እና ሞት የሚዳርጋቸው ዋንኛ ምክንያት ነውም ብሏል፡፡

ኦማር በሊቢያ ያሳለፈው ጊዜ በህይወቱ መቼም የማይረሳው ጥቁር ጠባሳ ያሳረፈበት የመከራ ጊዜ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ በጭነት መኪና 200 ህገ ወጥ ስደተኞች በከባድ መኪና ተጭነው ወደ ሊቢያ ሲያቀኑ ተጎድተዋል፡፡

ከሱዳን ሶማሊያ እና ኤርትራ የተውጣጡት ስደተኞች ከመንገድ ላይ 19ኙ ሲገደሉ 60ዎቹ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ባለፉት አራት አመታት 600 ሺህ ሰዎች ሜድትራኒያንን በማቋረጥ ወደ ጣሊያን ገብተዋል፡፡

ነገር ግን በዛው ልክ በሊቢያ ታግተው ያሉ ስደተኞች ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ነው፡፡

ምክንያቱ ደግሞ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ሳባርታ ከተማ የታጠቁ ሀይሎች ወደ አውሮፓ ስደተኞችን ጭነው የሚሄዱ ጀልባዎችን በመከልከላቸው የተነሳ ነው፡፡

በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት በሊቢያ በተለያዩ የህገ ወጥ አጋቾች ኢ ሰብአዊ በሆነ መንገድ ከ 400  እስከ 700 ሺህ የሚገመቱ ስደተኞችን በእስር ቤቶቻቸው አጉረዋቸው ይገኛሉ ማለታቸው ይታወሳል፡፡

አፍሪካም ሆነች መላው አለም ስደተኞቹ ወደ ቄያቸው በሰላም እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቦ አጥጋቢነቱ ጥያቄ ቢነሳበትም እንቅስቃሴው ተጀምሯል፡፡

ሶማሊያ በፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ትዕዛዝ አሁን 10 ያህል ስደተኞችን ስትመልስ በቅርቡ 30 የሚሆኑ ደግሞ ከትሪፖሊ ወደ ሞቃዲሾ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል

የሶማሊያ መንግስት በሊቢያ ያሉ ስደተኞች ወደ እናት አገራቸው እንዲመለሱ እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ነገር ግን ስደተኞቹ ወደ አውሮፓ መግባትን አማራጭ የሌለው መላ ነው ማለታቸው የጉዞውን አደገኛነት ግንዛቤ አስጨብጡ ተብለው የተላኩ የመንግስት ሰዎች እንዳልተሳካላቸው ተነግሯል፡፡

የሶማሊያ መንግስት አሁን ወደ ሞቃዲሾ ለተመለሱ ስደተኞች የስድስት ወር ወጫቸውን ለመሸፈን ቃል ገብቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ እና አለም አቀፉ የስደት ተቋም ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ መኖር የሚያስችላቸውን የህይወት ክህሎት ስልጠና መስጠት ጀምረዋል፡፡ ዘገባውን ከዘ ራይዚንግ ኦፍ አፍሪካ ላይ ተመለከትነው፡፡