በ2017 የዓለም አቀፍ ንግድ ጠንከራ አፈጻጻም ማሳየቱን ተገለጸ

የተጠናቀቀው በ2017 ዓለም አቀፍ ንግድ ጠንካራ አፈፃፀም ማሳየቱን ፓሪስ የሚገኘው የኢኮኖሚ ትስስር እና ልማት ድርጅት አስታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1948 የተመሠረተውና መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው የኢኮኖሚ ትስስር እና የልማት ድርጅት/ኦኢሲዲ/ 34 አባል ሃገራትንም በአባልነት አቅፏል፡፡

ድርጅቱ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ደህንነታቸውን የሚያሻሽሉ ፖሊሲዎችን ለማስተዋወቅ ፣ በዓለም አገራት ውስጥ ያለውን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ፣ የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲፈጠር ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡

ድርጅቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው የሸቀጣ ሸቀጦች ንግድ ረገድ ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ በተከታታይ ሰባት ዓመታት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል፡፡

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደየ አገራቱ የተላኩ  ምርቶች በ2 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ በአራተኛው ሩብ ዓመት ወደ አገር ውስጥ የገቡት ምርቶች ላይ ደግሞ 3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡   

የኢኮኖሚ ትስስር እና የልማት ድርጅት አባል ሃገራት የሆኑት እና የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ መሪ የሆኑት ጀርመን እና ፈረንሳይ ወደ ውጪ የላኩት ምርት በቅደም ተከተላቸው 2 ነጥብ 2 እና 3 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ማሳየታቸውን ድርጅቱ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

የናፍታ አባል ሃገራት ሪፖርት እንደሚያመላክተው ደግሞ ሪፖርቱ በሁሉም አባል ሃገራት እየጨመረ የሚሄድ የንግድ እንቅስቃሴ ይኖራል፡፡ በሪፖርቱ በአሜሪካ እና የውጪ ሀገራት የተደረገው የንግድ ልውውጥ በ 3 ነጥብ 5 በመቶ ሲጨምር ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ የገባው ምርት ደግሞ በ 5 ነጥብ 7 በመቶ አድጓል፡፡ በካናዳም ተመሳሳይ እድገት መመዝገቡን መረጃው ያመላክታል፡፡

እኤአ በ2017 ዓመቱን በሙሉ በነበረው የንግድ ልውውጥ በቡድን 20 አባል ሃገራት  ወደ ቡድኑ አገራት የላኳቸው ምርቶች መጠን በ10 በመቶ ጭማሪ ሲሳይ ወደ የተለያዩ አገራት ውጪ የላኳቸው ምርቶች ደግሞ 11 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የቡድን 20 አባል ሃገራት ባለፈው ዓመት ከተደረጉት ዓለም አቀፍ ንግድ መካከል 85 በመቶውን የሚሸፍኑ ሲሆን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን የሚያበረታታ እና ገበያ ሁኔታውም ጥሩ አዝማሚያ እንዲኖረው ማድረጋቸውን ነው ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ማመላከቱን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡