ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የአልሙኒየምና ብረት ምርቶች ላይ ከፍተኛ ግብር ሊጥሉ ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የአልሙኒየም እና የብረት ምርቶች ላይ ከፍተኛ ግብር ሊጥሉ መሆኑ ተገለጸ  ፡፡

አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የአሜሪካውያንን የሥራ እድል የሚያሳጣ እና ተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ንረት ይፈጥራል ሲሉ ተችተውታል፡፡

ቅድሚያ ለአሜሪካውያን ጥቅምን አስከብራለው የሚሉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሚያወጧቸው አዳዲስ ደንቦች በበርካታ ሃገራት ዘንድ ተቃውሞ እየገጠማቸው ይገኛል፡፡

ፕሬዝደንቱ አሜሪካ ፍትሃዊ ባልሆነ ንግድ እና ፖሊሲ ስትመራ እንደነበር እና  ለሃገሪቱ ይበጃታል ያሉትን አዲስ ህግ ይፋ ማድረጋቸውን የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡

ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ ፕሬዝዳንቱ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ብረቶች ላይ 25 በመቶ እና አልሙኒየሞች ላይ ደግሞ 10 በመቶ ታክስ እንደሚጥሉ ያሳያል፡፡

ድርጊቱን የተቃወሙ አካላት የአሜሪካውያንን የሥራ እድል የሚያሳጣ እና በተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ንረት ይፈጥራል ሲሉ ተችተውታል፡፡

ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና የአውሮፓ ህብረትም ውሳኔውን ተከትሎ አፀፋዊ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ነው መረጃው የሚያሳየው፡፡

ከግማሽ በመቶ በላይ የሚሆነውን ብረት የምታመርተው ቻይና ይፋዊ ምላሽ ባትሰጥም  አውስትራሊያ ግን ውሳኔውን በመቃወም የንግድ ግንኙነታችንን የሚያሻክር እና ሥራ አጥነትን የሚያስከትል ነው ብላለች፡፡

የጃፓኑ የንግድ ሚኒስትር ሂሮሺንጌ ሴኮ በበኩላቸው አሜሪካ ከጃፓን ጋር በመተባበር የምታስገባው አልሙኒየም እና ብረት ምንም ጉዳት እንደማያመጠባት አሳምናታለሁ ማለታቸውን ብሉምበርግ አስነብቧል፡፡፡፡

የጃፓኑ የመኪና አምራች ኩባንያ ቶዮታ የአክሲዮን ሽያጭ 2 በመቶ ዝቅ እንዳደረገው እና ውሳኔው በመኪና አምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ተጠቃሚዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ይሆናል ብሏል፡፡

ዩሮ ኒውስ ይዞት የወጣው ዘገባ ደግሞ ትራምፕ ምንም እንኳን ታክሱ አሜሪካውያንን የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ቢሉም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ግን የምርት ተጠቃሚዎችን፣ የተሸከርካሪ አምራች ድርጅቶችን በማዳከም አሜሪካውያንን የሥራ እድል እንዳያገኙ የሚጎዳ ነው ማለታቸውን ያትታል፡፡