ቻይና ባለፉት ሁለት ወራት ከኢንዱስትሪ ዘርፍ የ16 ነጥብ 1 በመቶ ትርፍ አገኘች

ቻይና ባለፉት ሁለት ወራት ከኢንዱስትሪ ዘርፏ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስነጻጸር የ16 ነጥብ 1 በመቶ ትርፍ እንዳገኘች አስታውቃለች፡፡

የቻይና ዋና ዋና የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስነጻጸር ያስመዘገቡት የትርፍ መጠን በ16 ነጥብ 1 ከመቶ ከፍ ያለ መሆኑን ከሀገሪቱ ብሄራዊ ስታስቲክስ ቢሮ የወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ አሀዝ  እንዱስትሪዎቹ በፈረንጆቹ 2017 ታህሳስ ወር ላይ ካስመዘገቡት የእድገት መጠን ጋር ስነጻጸር የ5 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው መረጃው የጠቆመው፡፡

መረጃው የተሰበሰበው በአመት ከ20 ሚሊዮን ዩአን በላይ የግብር ገቢ ከሚከፍሉ ትላልቅ ኩባንያዎች መሆኑ ሲነገር መረጃ ከተሰበሰበባቸው 41 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ደግሞ 29ኙ በተጠቀሱት ሁለት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ እንዳስመዝገቡ ተጠቅሰዋል፡፡

በቻይናው ስታስቲክስ ቢሮ መረጃ መሰረት ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ኢንዱስትሪዎች መካከል የመድሀኒት ፋብሪካዎች፣ የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎች እና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል የማዕድን ኢንዱስትሪ ገቢ ከጥር ወር እስከ የካቲት ባሉት ጊዚያት ውስጥ 42 ነጥብ 1 በመቶ የነበረ ሲሆን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ደግሞ 12 ነጥብ 5 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡

የስታትስቲክስ ባለሙያው ሂፒንግ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚገኘው ትርፍ ፈጣን ዕድገት ያሳየው ብቃትና ትርፍን ኢላማ አድርገው ኩባንያዎቹ በመንቀሳቀሳቸው እንደሆነ ገልጿል፡፡

በአለም አቀፍ ገበያ የቻይና ምርቶች ያላቸው ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱ ለቻይና ላኪዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ሲገለጽ አሁን ላይ አሜሪካና ቻይና በንግድ ዘርፉ የገቡት እሰጥ አገባ ግን የቻይና አመታዊ የንግደ ገቢ ላይ የበኩሉን ጫና ሊያሳድር ይችላል ተብሏል፡፡ (ሲ ጂ ቲ ኤን)