4ኛው አገር አቀፍ የምግብና መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪ በእግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ

ከ80 በላይ ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት 4ኛው አገር ዓቀፍ የምግብና መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ  በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተጀመረ።

ለአራት ቀናት በሚካሄደው በዚህ አውደ ርዕይ በምግብና መጠጥ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር መረጃ ለመለዋወጥና ከግብዓት አቅራቢዎችና መሳሪያ አምራቾች ጋር የሚገናኙበት እድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል። 

የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ በምግብና መጠጥ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች "ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት ዋና አካል በመሆናቸው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል። 

በዚህ ኤግዚቢሽን የተሳተፉ አካላት እንዳሉት ምግብነት ያላቸውን ምርቶች ለማምረት በተለይም ለብስኩቶችና ጣፋጮች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ወደ 90 በመቶ የሚሆኑት ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው የግብዓት እጥረት ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ግብዓቱ አገር ውስጥ እንዲመረት የውጭ ባለሀብቶችን የሚስቡ ስራዎች በባለ ድርሻ አካላት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘጋጀው ይህ አገር አቀፍ የምግብና የመጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም በተለይ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር መስክ ለተሳተፉት አምራች ኢንዱስትሪዎች ሰፊ አማራጭ ይከፍታል።(ኢዜአ)