ወጣትነት እሳት ነው ብረት አቅልጡበት…. ፋብሪካ ገንቡበት…. -ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ

ወጣትነት እሳት ነው፤ ይህን እሳት  ብረት አቅልጡበት…. ፋብሪካ ገንቡበት…. ወንዝ ጥለፉበት ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ከአዲስ አበባና ከመላው ሃገሪቱ ለተውጣጡ  ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

ከምንም በላይ ግን ይህንን እሳት ህይወትን ለማዳን ተጠቀሙበት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው በዚህ የውይይትና የምክክር  መደረክ ከ25 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢኮኖሚያችን እንደ ነዳጅ ባሉ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ሳይሆን በዜጎች ላብ እና በማይቋርጥ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ ነውም ብለዋል፡፡

በመሆኑም የዜጎችን በነጻ ነት መንቀሳቀስ የሚገታ ማንኛውም አጋጣሚ በኢኮኖሚያችን ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በሃገራችን የተከሰተው አለመረጋጋት በኢኮኖሚ አድገታችን  ላይ አንጻራዊ መቀዛቀዝን እንዳስከተለ ገልጸው አጋጣሚውን በበጎ ጎን በመውሰድ ለበለጠ እድገት በጋራ መስራት ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በንግግራቸው አንድነትን የሚያጠናክሩ እና ህዳሴያችን ሊያበስሩ የሚያችሉ በርካታ ጉዳዮችን ትኩረት የሰጡት  ሲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት  ከመንግስት ጎን እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡