ሁለተኛው የቻይና የንግድ ትርኢት ሳምንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው የቻይና የንግድ ትርኢት ሳምንት ትላንት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ተጀምሯል።

የቻይናው ኤምአይኢ ኩባንያና የኢትዮጵያው ፕራና ኤቨንትስ በጋራ ያዘጋጁት የንግድ ትርኢት ከሚያዚያ 25 እስከ 27 ቀን 2010 ዓም ድረስ የምቆይ ነው። 

በዘንድሮው የንግድ ትርኢት በዋናነት የቀረቡት የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና ማሽነሪዎች፣ የግብርና መሳሪያዎች፣ ለኤሌክትሪክና ለማዕድን ስራ የሚያገለግሉ መሳሪዎች፣ የምግብ ማቀነባበሪያ ማሽኖችና የመብራትና የኢነርጂ መሳሪያዎች ናቸው።

የንግድ ትርኢቱ አስተባባሪ የፕራና ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በሁለተኛው የቻይና የንግድ ሳምንት ወደ 50 የሚጠጉ የቻይና ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውንም እንደሚያስተዋውቁ ተናግረዋል።

'የቻይና ምርት ጥራት እንደሌለው ተደርጎ ይታመናል' ያሉት አቶ ነብዩ ያንን አስተሳሰብ ሊቀርፍ የሚችል ጥራት ያለው ምርት መኖሩን ለማሳየት የንግድ ትርኢቱ ጠቃሚ መድረክ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከንግድ ትርኢቱ ጎን ለጎን በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ባለኃብቶች ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የንግድ አጋርነት መፍጠር የሚያስችላቸውን ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና ቻይና በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በባህል፣ በትምህርትና በጤና እንዲሁም በአለም አቀፋዊ ጉዳዮች ውጤታማ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት መስርተዋል።

የቻይና የንግድ ሳምንት ከኢትዮጵያ ውጪ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሞሮኮ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በኢራንና በጋና እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የንግድ ትርኢቱ በስኬት መጠናቀቁ ይታወሳል። (ኢዜአ)