ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 27ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ኢትዮ-ቴሌኮም  በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአጠቃላይ 27 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ ።

ኢትዮ-ቴሌኮም በተጠቀሱት ወራት የተሻለ የአገልግሎትና የምርት አማራጭ በማቅረብ 29 ነጥብ 95 ቢሊየን ብር  ገቢ ለማግኘት አቅዶ 27 ነጥብ 79 ቢሊየኑን በማግኘት የእቅዱን 93 በመቶ  እንዳሳካም ለዋልታ በላከው መግለጫው ጠቅሷል፡፡

ኢትዩ ቴሌኮም በ2010 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የደንበኞቹን ቁጥር ከ66 ሚሊየን በላይ መድረሱንም ገልጿል ፡፡

የሞባይል ደንበኞቹ ቁጥር ከ64 ሚሊየን በላይ እንደደረሰና ይህም ከእቅድ አንጻር የ97 በመቶ ዕድገት እንዳለው ነው ኩባንያው ለዋልታ ቴሌቭዥን በላከው መግለጫ ያስታወቀው ፡፡

በሌላ በኩል የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 ነጥብ 2 ሚሊየን መድረሱንና  የኢንተርኔት እና ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥርም 16 ሚሊየን መድረሱን ጠቁሞ፥ ከእቅድ አንፃር የ75 እና 77 በመቶ እድገት መታየቱን  ገልጿል፡፡  

በዘጠኝ ወራት ውስጥ 26 አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ታቅዶ 19 አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ የዕቅዱን 73 በመቶ አሳክቷል፡፡

ኩባንያው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያስመዘገበውን አመርቂ ውጤት ለማስቀጠል እና የአገልግሎት ዘርፎቹን ብቃት ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡