አየር መንገዱ በ100 አውሮፕላኖች አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን ተገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ100 አውሮፕላኖች አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ አቪዬሽን ታሪክ የመጀመሪያው የአየር መንገድ ሊሆን ነው።

የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በግዢ ያዘዘውን ቦይንግ 787 900 ሲረከብ በአፍሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 100 አውሮፕላን ያለው አየር መንገድ እንደሚሆን አየር መንገዱ አስታውቋል።

ታሪካዊው ሁነት አየር መንገዱ በሁሉም መስኮች በአፍሪካ የአቪዬሽን አገልግሎት መሪነቱን የሚያሳይና በኢቪዬሽን ቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም ሚናውን የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ 100 አውሮፕላኖችን መጠቀም ላይ ለመድረስ መቃረቡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

በ100 አውሮፕላኖች አገልግሎት የመስጠት አቅም ላይ መድረሱ አየር መንገዱ በአፍሪካ አቪዬሽን ያለውን ታሪክ የሚያስቀጥልና ፈጣን፣ ትርፋማና ዘላቂነት ባለው መልኩ በስኬት እየተገበረ ያለው ራዕይ 2025 ስራን የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 100 ዘመናዊ አውሮፕላኖችን መጠቀም መቻሏ የአገሪቱ የአቪዬሽን ዘርፍ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያመላክት እንደሆነ አየር መንገዱ ገልጿል።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሆኑትን ቦይንግ 787 እና ኤርባስ 350 አውሮፕላኖችን በመግዛት ለተሳፋሪዎች ምቹ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና ደንበኞቹን አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ተግባር በስፋት እያከናወነ እንደሆነ አስታውቋል።

የ100 አውሮፕላን አገልግሎት የመስጠት የ2025 ራዕይ ቀድሞ በመሳካቱ ማሻሻያ በማድረግ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን በመግዛት በአፍሪካ ያለውን የጉዞ ፍላጎት ለማሟላትና የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ፍሰቱን በማመቻቸት ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ትስስር እንደሚሰራም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት ከ110 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዳሉት የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡