ከአውሮፕላን ነዳጅ ውጭ የሁሉም ነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በሰኔ ወርም ባለበት እንደሚቀጥል ተገለጸ

በግንቦት ወር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ከግንቦት 29 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ድረስ  ባለበት እንደሚቀጥል የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ንግድ ሚኒስቴር ለጣቢያችን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በስተቀር የሌሎች ነዳጅ ምርቶች ዋጋ ባለበት የሚቀጥል ይሆናል።

‘በግንቦት ወር የነበረው የነዳጅ ምርቶች  የዓለም ዋጋ ከባለፈው  ወር ጋር ሲነጻጸር በሁሉም የነዳጅ ምርቶች ላይ ጭማሪ አሳይቷል’ ያለው ሚኒስቴሩ፤ የአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማስቻል ጭማሪ አለመደረጉን አመልክቷል።

የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በግንቦት ወር ይሸጥበት ከነበረው 23 ከ 80 ብር በዓለም ወቅታዊ ዋጋ አማካይነት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት 2 ብር ከ11 ሳንቲም  በመጨመር በሊትር ብር 25 ከ91 ሳንቲም እንዲሆን ተደርጓል።

በዓለም ገበያ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ የዋጋ ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ በመግለጫው  አመላክቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመስከረም 2001 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በየወሩ እንዲከለስ መመሪያ ማስቀመጡ ይታወሳል።