የሐምሌ ወር የዋጋ ግሽበት 14 በመቶ ሆኖ መመዝገቡ ተገለጸ

የሐምሌ ወር አጠቃላይ ሀገራዊ የዋጋ ግሽበት 14 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለዋልታ በላከው መግለጫ መሠረት የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር 0 ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ ማስመዝገቡን ጠቁሟል።

በሐምሌ ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት 16 ነጥብ 7 ሆኖ ሲመዘገብ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ደግሞ 10 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከባለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በእህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመም ዋጋ ላይ ጭማሪ የተመዘገበ ቢሆንም በዳቦ፣ ሥጋ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ አይብ፣ ዕንቁላል ፣ስኳር፣ ማርና ቼኮሌት ላይ መጠነኛ ቅናሽ ታይቷል።  

ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል ያደረጉት፦ በአልባሳትና ጫማ፣ የቤት ማደሻ እና ማስዋቢያ ቁሳቁሶች፣ የኃይል ፍጆታዎች እንዲሁም በሆቴሎች የሚወሰዱ ምግቦችና መጠጦች ላይ ጭማሪ በመታየቱ ነው ተብሏል።

በዚህ ወር የነበረው የዋጋ ጭማሪ ባለፉት ወራት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር መረጋጋት መሳየቱን ኤጀንሲው አስታውቋል።