ኬንያ በባለፈው ፈረንጆቹ ዓመት ከቱሪዝም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች

ኬንያ በባለፈው ፈረንጆቹ ዓመት 2018 ከቱሪዝም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ታውቋል፡፡

ቱሪዝም በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ሃገራት ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙበት እና የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ የሚልኩበት ቁልፍ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ለቱሪዝም ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ ይታያል፡፡

ጎረቤት ሃገር የሆነችው ኬንያ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት 2018 የቱሪዝም ገቢዋ በፊት ስታገኝ ከነበረው ገቢ በ31.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡  በተለይ ከ2017 የምርጫ ጊዜ በኋላ ወደ ሃገሯ የመጡት የቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ነው ሲጂቲኤን በዘገባው ያስነበበው፡፡

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ኬንያን የጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በ2018 በቱሪዝሙ ዘርፍ የተገኘው 157.3 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 15 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲሆን ከዓመታት በፊት የነበረው ከቱሪስቶች የምታገኘው ዓመታዊ ገቢዋ ከ120 ቢሊዮን ሽልንግ እንደማይዘል ነው የተገለጸው፡፡

የኬንያ ቱሪዝም ካቢኔ ዋና ጸሃፊ ሆኑት ናጂብ ባላላ እንደገለጹት በዘርፉ ከፍተኛ እድገት ሊታይ የቻለው መንግስት ለቱሪዝም የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና የቱሪዝም ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ገበያ እንዲያገኙ ማድረጉ ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የመንግስት ድርጅቶች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት በመስራታቸው አመርቂ ውጤት ሊገኝ ተችሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2017 በኬንያ በነበረው የምርጫ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የቱሪስቶች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከምርጫው ቡሃላ የነበረው አለመረጋጋት ከሰከነ ቡኃላ ግን መንግስት በዘርፉ ከፍተኛ ስራ በመስራቱ የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም ኬንያን ከጎበኟት ቱሪስቶች መካከልም 225 ሺ 157 አሜሪካውያን ይገኙበታል፡፡

ይህም ከተለያዩ ሃገራት ለጉብኝት ከመጡ ውጭ ሃገራት ዜጎች አንፃር አሜሪካውያን ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ እንደማለት ነው፡፡ ከአሜሪካውያን ቀጥሎ ቻይናውያን ጎብኝዎች ደግሞ በፊት ከነበረው በአራት በመቶ በመጨመር 81 ሺ 709 ጎብንኝዎች የኬንያን የቱሪዝም መስህቦችን በመጎብኘት የሃገሪቷን የቱሪዝም ዋነኛ የገቢ ምነጮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡/ሲጂቲኤን/