አውስትራሊያ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እያስተናገደች ነው

አውስትራሊያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እያስተናገደች መሆኑ ተገለፀ ፡፡

በሙቀቱ ምክንያት የውሃ አካላት እየሞቱ ሲሆን ሙቀቱ አሁን ካለው በላይ ሊቀጥል እንደሚችል የሃገሪቱ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገልጿል፡፡

በዓለም የሙቀት መጠን መጨመር እና ያልተለመደ ተቀያያሪ የአየር ፀባይ ምክንያት ከባድ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የተባሉ ምልክቶች እየታዩ መጥተዋል፡፡

በረዶአማ ስፍራዋ ቀልጦ አረንጓዴ ከታየባት አንታርቲካ እስከ በጎርፍ እና ሰደድ እሳት እየተጠቁ ካሉ በርካታ የዓለም ሃገራት ድረስ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡

በአወስትራሊያ የተከሰተው ይህው ከፍተኛ የሙቀት መጠንም አንዱ የአየር ፀባይ ለውጡ ውጤት ነው፡፡

የሲኤን ኤን ዘገባ እንደሚያሳው በሃገሪቱ በተለያዩ ከተሞች የተከሰተው የተለያየ መጠን ያለው የአየር ፀባይ ከ40 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ በማስመዝገብ ስድስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡

በአወስትራሊያ ታሪክ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው የሙቀት መጠን በሰሜን ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍል በምትገኘው ማርብል ባር ከተማ ላይ እሁድ እለት የሙቀት መጠኑ 49.1 ዲግሪ ሴንትግሬድ መድረሱን እና ለተከታታይ 20 ቀናትም የሙቀት መጠኗ ከ40 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ ሆኖ መቆየቱን ዘገባው ጠቅሷል፡፡

በደቡብ አወስትራሊያ ኒው ሳውዝ ዌልስ፣ እና ቪክቶሪያ የሙቀት መጠን 48 ነጥብ 9 ዲግሪ ሴንትግሬድ እና በአጉስታ ደሴት 47 ነጥብ 8 በአንዳሙካ 46 ነጥብ 4 በመድረሱ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በሙቀት መጨመር ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ አሳዎች ሞተው መገኘታቸውን እና ሙቀቱ ከዚህ በላይ የሚጨምር ከሆነ የሌሎች የውሃ አካላት እጣ ፈንታም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው፡፡

የአካባቢያዊ ጥበቃ አቀንቃኞች ለተፈጠረው ችግር የሃገሪቱን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ደካማ የውሃ አያያዝ እና ከበቂ በላይ ውሃ ለመስኖ ማዋል ለዓሳዎቹ መሞት ምክንያት ነው ብለዋል፡፡